አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በጀርመን ሞስሌ ወንዝ ዳርቻ የሚገኝ አንድ ሆቴል በከፊል በመደርመሱ የአንድ ሰው ህይወት ሲያልፍ ጥቂቶች ላይ ከባድ የአካል ጉዳት መድረሱ ተመላክቷል፡፡
ስምንት ሰዎች ደግሞ መውጫ አጥተው በወደቀው የህንፃ ክፍል ውስጥ እንደሚገኙ የአካባቢው ፖሊስ አስታውቋል።
የሟች አስከሬን ቢገኝም እስካሁን ማውጣት አለመቻሉን ያስታወቀው ፖሊስ÷ መውጫ ካጡ የተወሰኑ ሰዎች ጋር ግን ግንኙነት መፍጠር መቻሉን ገልጿል።
ከደረሰው አደጋ አንፃር የነፍስ አድን ሥራው ትልቅ ጥረት የሚጠይቅ ነው ያለው መግለጫው÷ ወደ ህንጻው መግባት የሚቻለው በድንገተኛ አደጋ ምላሽ ሰጪዎች ከፍተኛ ጥንቃቄ ብቻ መሆኑን አመላክቷል።
በሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን የተጋሩ ምስሎች÷ የሕንፃው ጣሪያ ጫፍ ወደ ኋላ አዘንብሎና ገሚሱም የምድር ወለል ክፍሎች ፈራርሰው አሳይተዋል።
በህንፃው ላይ አደጋው ሲደርስ 14 ሰዎች ውስጥ እንደነበሩና አምስቱ ምንም ጉዳት ሳይደርስባቸው ማምለጥ እንደቻሉ መርማሪዎች መናገራቸውን ሬውተርስ ዘግቧል።
በህንፃው ላይ የደረሰውን ጉዳት የተመለከቱ 31 ጎረቤቶችም ለደህንነታቸው ሲሉ ቤታቸውን ለቀው መውጣታቸውን ፖሊስ አስታውቋል።