ዓለምአቀፋዊ ዜና

ሂዝቦላህ በእስራኤል ላይ በሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃት መፈፀሙን ገለጸ

By Amele Demsew

August 06, 2024

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሊባኖሱ ታጣቂ ቡድን ሂዝቦላህ ወደ ሰሜናዊ እስራኤል ተከታታይ የሰው አልባ አውሮፕላን እና የሮኬት ጥቃቶችን መፈፀሙን ገለጸ፡፡

እስራኤል ባለፈው ሳምንት የቡድኑን ከፍተኛ አዛዥ መግደሏን ተከትሎ እየተጠበቀ ያለው የበቀል እርምጃ ገና ይቀጥላል ሲልም አስጠንቅቋል።

ሄዝቦላህ በሰሜን እስራኤል በአክሬ አቅራቢያ የሚገኙ ሁለት የጦር ሰፈሮችን በሰው አልባ አውሮፕላኖች ማጥቃት መጀመሩን እና በሌላ ቦታ በእስራኤል ወታደራዊ ተሸከርካሪ ላይ ጥቃት መሰንዘሩንም ተናግሯል።

የእስራኤል ጦር በበኩሉ ከሊባኖስ የተወነጨፉ በርካታ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን መለየታቸውን እና አንደኛው መክሸፉን አስታውቋል።

የህክምና ባለስልጣናትም ጉዳት የደረሰባቸው ሰባት ሰዎች ከአካባቢው ለቀው በደቡባዊ ድንበር ከተማ ናሃሪያ ወደ ሚገኝ ሆስፒታል መወሰዳቸውን፤ አንዱም አስጊ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

የእስራኤል ጦር እንደገለጸው በርካታ ንጹሃንን ያቆሰለው አደጋ የደረሰው ሰው አልባ አውሮፕላኖችን ለመምታት የተወነጨፈ ተተኳሽ ኢላማውን ስቶ መሬት በመውደቁ ነው፡፡

ይሁንና ክስተቱ አሁንም በምርመራ ላይ እንደሚገኝ አመላክቷል፡፡

የእስራኤል ጦር በሰጠው መግለጫ በአክሬ አካባቢ የማንቂያ ደወል ድምፅ እንደተሰማና ነገር ግን ያ የውሸት ማንቂያ ሆኖ መገኘቱን ገልጿል፡፡

የአየር ኃይሉ በደቡብ ሊባኖስ ሁለት የሂዝቦላ ተቋማትን መምታቱንም ተናግሯል።

የሂዝቦላህ አዛዥ ፉአድ ሹክር እና  ባለፈው ሳምንት በቴህራን ለተገደለው የፍልስጤም ታጣቂ ቡድን ሃማስ መሪ ኢስማኤል ሃኒዬህ አጸፋ  እንደሚመልሱ ሂዝቦላህና ኢራን ዛቻ መሰንዘራቸውን ተከትሎ መካከለኛው ምስራቅ ወደ ሙሉ ጦርነት ሊገባ ይችላል የሚል ስጋት እየጨመረ መጥቷል።

ለኮማንደር ፉአድ ሹክር ግድያ የሚሰጠው ምላሽ ገና አልተጀመረም ሲሉ አንድ የሂዝቦላህ ምንጭ መናገራቸውን ሬውተርስ ዘግቧል፡፡