የሀገር ውስጥ ዜና

ባንክ በመዝረፍና ለሽብር ቡድን ድጋፍ በማድረግ ወንጀል የተከሰሱት የዋስትና መብታቸው ውድቅ ተደረገ

By Feven Bishaw

August 06, 2024

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ባንክ በመዝረፍ፣ ግለሰቦችን በመግደልና ለሸኔ የሽብር ቡድን ድጋፍ በማድረግ የሽብር ተግባር የተከሰሱት እነ መርጋ ሙሉነህ በንቲ  (ጃል ሎላ) የዋስትና ጥያቄያቸው ውድቅ ተደርጓል።

የዋስትና ጥያቄያቸውን ውድቅ ያደረገው የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ የህገ-መንግስትና በህገ-መንግስት ስርዓት ላይ የሚፈጸሙ የወንጀል ጉዳዮችን የሚመለከተው ችሎት ነው።

የዋስትና ጥያቄያቸው ውድቅ የተደረገባቸው ተከሳሾች መርጋ ሙሉነህ በንቲ ( ጃል ሎላ) ፣ ገለታ በቀለ ቡልቻ፣መገርሳ ሶማ ዶጃ፣ዋቅጅራ ጌታቸው መርዳሳ፣ ዋዳ ጌታቸው ጊንዳሳ እና ሳሙኤል ኢስራኤል ቶማስ የተባሉ ግለሰቦች ናቸው።

የፍትህ ሚኒስቴር የፌደራል የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ህግ በስድስት ግለሰቦች ላይ የተሳትፎ ደረጃቸውን ጠቅሶ ከአንድ ሳምንት በፊት የሽብር ወንጀል ክስ አቅርቦባቸው እንደነበር ይታወሳል።

በዚህም አንደኛው ክስ በ1ኛ ተከሳሽ መርጋ ሙሉነህ በንቲ ( ጃል ሎላ) ላይ በቀረበው ክስ እንደተመላከተው ግለሰቡ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪነት የተፈረጀውን የሸኔ የሽብር ቡድን አባል በመሆን  ከጳጉሜ ወር 2011 ዓ.ም ጀምሮ በሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞን፣ አባይ ጮመን ወረዳ ባቱ በሚባል አካባቢ ወታደራዊ ስልጠና ወስዶ በኦሮሚያ ክልል በሆሮጉድሩ ወለጋ ዞን፣ በምዕራብ ወለጋ፣ በጂማ ዞንና በምስራቅ ወለጋ ዞን  ከሌሎች ግብረአበሮቹ ጋር በመሆን ለሽብር ወንጀል  ተግባር ሲንቀሳቀሱ እንደነበር  ጠቅሶ ዐቃቤ ህግ በክሱ አስፍሯል።

በተለይም መስከረም 12 ቀን 2015 ዓ.ም ተከሳሹ ከሌሎች ግብረአበሮቹ ጋር በመሆን በሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞን ዳርዳጋ ጃርቴ ወረዳ  በመንቀሳቀስ የፀጥታ አካላት ላይ በመተኮስ የወረዳውን አስተዳደር ጽ/ቤት ንብረት እና የሌላ የፀጥታ አካላት ተሽከርካሪዎችን፣ሞተር ሳይክሎችን  በማቃጠል፣የተለያዩ  ከንግድ ባንክ አሊቦ ቅርጫፍና አዋሽ ባንክን ካዝና በመስበር 10 ሚሊየን 658 ሺህ 783 ብር መዝረፋቸው በክሱ ተመላክቷል።

ሌሎችም ተከሳሾች ለሽብር ቡድኑ የጦር መሳሪያ፣የተለያዩ የሎጀስቲክ ድጋፎችን ሲያደርጉ እንደነበር በክሱ ላይ የተጠቀሰ ሲሆን÷ 5ኛ እና 6ኛ ተከሳሾች ደግሞ ለአንደኛ ተከሳሽ ስም የአዲስ አበባ በአራዳ ክ/ከ  ወረዳ 2 ስም ሀሰተኛ የነዋሪነት መታወቂያ አዘጋጅተው ሰጥተዋል የሚል ክስ ነው።

በዚህ መልኩ የቀረበባቸው ክስ ከደረሳቸው በኋላ በጠበቃቸው አማካኝነት ዋስትና  እንዲፈቀድላቸው የጠየቁ ሲሆን÷በከሳሽ ዐቃቤ ህግ በኩል ዋስትና ሊፈቀድላቸው አይገባም በማለት ተከራክሮ ነበር።

የግራ ቀኝ ክርክሩን የመረመረው ፍርድ ቤቱ ዛሬ ከሰዓትበኋላ በነበረው ቀጠሮ 1ኛ ተከሳሽ ከተከሰሰበት ድንጋጌ አንጻር እና የቀረበበት ክስ  የሰው ህይወት የጠፋበትና ጉዳት የደረሰበት መሆኑ ተጠቅሶ  የጠየቀው የዋስትና ጥያቄ ውድቅ ተደርጓል።

ፍርድ ቤቱ ከ2ኛ እስከ 6ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱት ተከሳሾች ደግሞ በዋስ ቢወጡ የዋስትና ግዴታቸውን አክብረው ሊቀርቡ አይችሉም የሚለውን ግምት በመያዝ የጠየቁትን የዋስትና ጥያቄ ውድቅ በማድረግ መዝገቡን ለጥቅምት 8 ቀን 2017 ዓ.ም ተቀጥሯል።

በታሪክ አዱኛ