አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የጦር ሀይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ እና ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄኔራል አበባው ታደሰ በመከላከያ ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን የኤሌክትሮኒክስ ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ የራዲዮ መገጣጠሚያ ፋብሪካን መርቀው ከፍተዋል፡፡
ፊልድማርሻል ብርሃኑ ጁላ ወታደራዊ ራዲዮው በዓለም ላይ የመጨረሻው የዲጂታል ደረጃ ራዲዮ መሆኑን ገልጸው÷ይህንን እዉን ለማድረግ የቻይናው ሀይቴራ ኩባንያ እና የመከላከያ ኢንጅነሪንግ ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን አመራሮች ላበረከቱት አስተዋፅኦ አመስግነዋል።
የመከላከያ ኢንጅነሪንግ ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ሀይለማርያም በበኩላቸው ÷ፋብሪካው የመካከለኛና የረጅም ርቀት ወታደራዊ ራዲዮኖችን የሚያመርት መሆኑን ጠቅሰው ከወታደራዊ ራዲዮኖች ባለፈ ለሲቪል አገልግሎት የሚውሉ ራዲዮኖችን የሚያመርት ፋብሪካ እንደሆነ ተናግረዋል።
የመከላከያ ተቋም ከዚህ በኋላ ምንም አይነት የግንኙነት ራዲዮ ከውጭ ሀገር እንደማይገዛና ሙሉ በሙሉ በተመረቀው የራዲዮ ፋብሪካ እንደሚሸፈን ያስታወቁት ዋና ዳይሬክተሩ÷ ፋብሪካው በዓመት 32 ሺህ ራዲዮኖችን የማምረት አቅም እንዳለውም ገልፀዋል።
የኤሌክትሮኒክስ ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ ስራ አስኪያጅ ኮሎኔል ዘውዱ አለፈ÷ በፋብሪካው የቴክኖሎጂ ሽግግር የተካሄደበት እና በሜጄር ጄኔራል ሙሉጌታ ቡሊ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የተማሩ የቴክኒክ ሙያተኞች በመገጣጠሙ ተግባር ይሳተፉበታል ብለዋል።
ወታደራዊ ራዲዮው እጅግ ዘመናዊ ፣ በኢትዮጵያ ማንኛውም የአየር ፀባይ ያለእንከን የሚሰራ ፣ ለአያያዝ ቀላል፣ ለየትኛውም ግዳጅ የሚመች እንደሆነና የውጭ ምንዛሬ የሚያስገኝ መሆኑንም በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ መገለፁን ከመከላከያ ሠራዊት ፌስቡክ ገፅ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡