Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

አቶ ጥላሁን ከበደ በክልሉ እየተከሰተ ያለውን የተፈጥሮ አደጋ ለመከላከል እየተሠራ መሆኑን ገለጹ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች እየተከሰተ ያለውን የተፈጥሮ አደጋ ለመከላከል ሕዝቡን በማሳተፍ እየተሠራ ነው ሲሉ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ጥላሁን ከበደ ገለጹ፡፡

ርዕሰ መሥተዳድሩን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች በወላይታ ዞን ካዎ ኮይሻ ወረዳ ጤፓ ቀበሌ ተገኝተው ትናንት በመሬት መንሸራተት ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች አጽናንተዋል።

በዚሁ ወቅትም በክልሉ በቅርቡ በጎፋ ዞን በደረሰው ከባድ የተፈጥሮ አደጋ በርካታ ወገኖችን በሞት ባጣንበት ወቅት የተከሰተ ተጨማሪ አደጋ መሆኑ ልባችንን ሰብሮታል ያሉት አቶ ጥላሁን÷ ቤተሰቦቻቸውን ላጡ ወገኖች መጽናናትን ተመኝተዋል ።

መሠል አደጋ በአካባቢው ተከስቶ ተጨማሪ ጉዳት እንዳይደርስ ማኅበረሰቡ እራሱንና ቤተሰቡን ከአደጋ ስጋት እንዲከላከል አሳስበዋል።

በአደጋው ለተጎዱና ለተፈናቀሉ ወገኖች ተገቢውን ድጋፍ ማድረግ እንደሚያስፈልግም አስገንዝበዋል፡፡

በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች እየተስተዋለ ያለውን የተፈጥሮ አደጋ በተገቢው መንገድ ለመከላከል የክልሉ መንግስት ሕዝቡን በማስተባበር እየሠራ መሆኑንም አረጋግጠዋል፡፡

በማስተዋል አሰፋ

Exit mobile version