የሀገር ውስጥ ዜና

አቶ ታዬ ደንደአ ከቀረቡባቸው ክሶች በሁለቱ ነጻ ሲባሉ በአንዱ እንዲከላከሉ ብይን ተሰጠ

By ዮሐንስ ደርበው

August 06, 2024

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሰላም ሚኒስትር ዴዔታ የነበሩት ታዬ ደንደአ ከቀረቡባቸው ሦስት ክሶች መካከል በ1ኛ እና በ2ኛ ክስ ነጻ የተባሉ ሲሆን በ3ኛው ክስ እንዲከላከሉ ብይን ተሰጠ፡፡

ብይኑን የሰጠው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የሕገ-መንግሥትና በሕገ-መንግሥት ሥርዓት ላይ የሚፈጸሙ የወንጀል ጉዳዮችን የሚመለከተው ችሎት ነው።

የፍትሕ ሚኒስቴር የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ በአቶ ታዬ ደንደአ ላይ ሦስት ክሶችን ማለትም በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀጽ 251/ሐ እና አንቀጽ 257/ሰ ሥር የተመላከተውን ድንጋጌ እና የጦር መሳሪያ አዋጅን መተላለፍ የሚል ክስ አቅርቦ ነበር።

ቀርቦ በነበረው ዝርዝር ክስ ላይም ተከሳሹ የሰላም ሚኒስትር ዴዔታ ሆነው ሲሠሩ የሀገር፣ የመንግሥትና የሕዝብን ደኅንነት ማስጠበቅ ብሎም ማረጋገጥ ሲገባቸው፤ ይህን ወደጎን በመተው የሽብር ቡድኖችና ፀረሰላም ኃይሎችን የሚደግፉ ፕሮፓጋንዳ መልዕክቶችን በስማቸው በከፈቱት ማኅበራዊ ትስስር ገጽ ሲያስተላልፉ ነበር የሚለው ይገኝበታል፡፡

በተጨማሪም ፈቃድ ሳይኖራቸው የጦር መሳሪያ አዋጁን በመተላለፍ ታኅሣስ 1 ቀን 2016 ዓ.ም ከረፋዱ 5 ሠዓት ላይ በልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 በሚገኝ ቤታቸው ውስጥ በተደረገ ብርበራ አንድ ታጣፊ ክላሽንኮቭ መሳሪያ፣ ሁለት የክላሽንኮቭ ካዝና እና 60 ተተኳሽ ጥይት ተገኝቶባቸዋል የሚል ክስ መቅረቡ ይታወሳል።

ክሱ ከደረሳቸው በኋላም ተከሳሹ “የጻፍኩት ጽሑፍ ፕሮፓጋንዳ አይደለም፤ ወንጀል አልፈጸምኩም” ሲሉ የዕምነት ክህደት ቃል መስጠታቸውን ተከትሎ፤ ዐቃቤ ሕግ ምስክር እንዲሰማ ባቀረበው ጥያቄ መሰረት የምስክር ጭብጥ በችሎት ካስመዘገበ በኋላ የሁለት ግለሰቦች የምስክር ቃላቸውን አሰምቶ ነበር።

ፍርድ ቤቱም የተሰሙ ምስክሮችን ቃልና በማኅበራዊ ትስስር ገጽ ተላልፈዋል የተባሉ የፕሮፓጋንዳ መልዕክቶችን የያዙ የሠነድ ማስረጃዎችን መርምሮ ዛሬ ብይን ሰጥቷል።

በዚህም ተመሳሳይነት ያላቸውን ንግግሮችና ጽሑፎች ዐቃቤ ሕግ የተለያየ ክስ አድርጎ 1ኛ እና 2ኛ ብሎ ማቅረቡ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 61ን ያላገናዘበ ነው ብሏል ፍርድ ቤቱ፡፡

በዚሁ ክስ ዝርዝርም ተከሳሽ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ያጋሩትና ለቢቢሲ አፋን ኦሮሞ የሰጡት ቃለ መጠይቅ ሐሳብን የመያዝና የመግለጽ ሕገ-መንግሥታዊ መብትን በመጠቀም ሐሳብን ከመግለጽ ያለፈ፣ የሕዝብን ደኅንነት፣ ሰላምን፣ የሕዝብን የሞራል ሁኔታ እንዲሁም የዜጎችን ነጻነት የሚነካ ሆኖ አላገኘነውም በማለት መከላከል ሳያስፈልግ በ1ኛ እና 2ኛ ክስ በወ/መ/ስ/ሕግ ቁጥር 141 መሰረት በነጻ አሰናብቷቸዋል።

እንዲሁም በ3ኛው ማለትም ታኅሣስ 1 ቀን 2016 ዓ.ም ከረፋዱ 5 ሠዓት ላይ በልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው በተደረገ ብርበራ አንድ ታጣፊ ክላሽንኮቭ ከሁለት የክላሽንኮቭ ካዝና እና ከ60 ጥይት ጋር ተይዞባቸዋል ተብሎ የቀረበውን ክስ በተመለከተ መሳሪያው መገኘቱ በዐቃቤ ሕግ ማስረጃ የተረጋገጠ መሆኑን በመጥቀስ ፍርድ ቤቱ በወ/መ/ስ/ሕግ ቁጥር 142/1 መሰረት በተከሰሱበት የጦር መሳሪያ አዋጅ 1177/2012 አንቀጽ 4 ንዑስ ቁጥር 1 እና በአንቀጽ 22 ንዑስ ቁጥር 3 የሕግ ድንጋጌ ሥር ክሱን እንዲከላከሉ ብይን ሰጥቷል፡፡

ከብይኑ በኋላም ተከሳሹ እንዲከላከሉ በተበየነበት 3ኛ ክስ የዋስትና መብት ተፈቅዶ በውጭ ሆነው ጉዳዩን ለመከታተል እንዲፈቀድላቸው ጠይቀዋል።

ዐቃቤ ሕግም ተከላከል የተባለበት ድንጋጌ ከ8 ዓመት እስከ 20 ዓመት የሚያስቀጣ ድንጋጌ በመሆኑና የዋስትና ግዴታውን አክብሮ ላይቀርብ ይችላል በማለት የዋስትና መቃወሚያ መከራከሪያ አቅርቧል።

ፍርድ ቤቱ በበኩሉ የዋስትና ጥያቄንው መርምሮ ከሠዓት በኋላ በነበረ ቀጠሮ ተከሳሹ በዋስ ቢወጣ የሕግ ግዴታውን አክብሮ ሊቀርብ አይችልም የሚለውን ግምት በመያዝ የዋስትና ጥያቄውን ውድቅ አድርጎታል፡፡

ከዚህ በኋላም ተከሳሹ አንድ ክላሽንኮቭ ይዟል ተብዬ ዋስትና መከልከሌ ተገቢ አይደለም የሚል ሐሳብ ያቀረቡ ሲሆን÷ ፍርድ ቤቱም ብይኑ ከሕግ አንጻር የተሰጠ መሆኑን አስረድቷል፡፡

በጠበቆቼ ላይ ጫና በማሳደር እንዳይቆሙልኝ ተደርጌያለሁ በማለት ተከሳሹ አቤቱታ ያቀረቡ ሲሆን÷ ፍርድ ቤቱ ጠበቆቹ መሥራት አልቻልንም በማለት በራሳቸው እንዲያመለክቱ በመግለጽ፤ የመንግሥት ተከላካይ ጠበቃ ለተከሳሹ ሊቆም ይችላል በማለት ገልጿል፡፡

ፍርድ ቤቱ ተከሳሹ ተከላከል በተባሉበት 3ኛ ክስ ላይ የመከላከያ ማስረጃ ለመጠባበቅ ለጥቅምት 8 ቀን 2017 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

በታሪክ አዱኛ