አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ትግበራው የገንዘብና የፊሲካል ፖሊሲ አቅምን የሚገነባና የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ሥርዓትን የሚያዘምን መሆኑን የገንዘብ ሚኒስቴር እና የፕላንና ልማት ሚኒስቴር የተለያዩ የሥራ ኃላፊዎች ገለጹ።
መንግሥት ቀጣይነት ያለው ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ለማስመዝገብና የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ትግበራን በተሟላ መልኩ በይፋ ማስጀመሩ ይታወቃል።
በገንዘብ ሚኒስቴር የፊሲካል ፖሊሲ አማካሪ መዝገቡ አምሃ÷ የፖሊሲው ሙሉ ትግበራም የሀብት ብክነትን በማስቀረት ምርታማነትን በማሳደግና ኢንቨስትመንትን በማሳደግ ረገድ አስተዋጽዖው የላቀ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የውጭ ምንዛሪና የክፍያ ሚዛንን እንዲሁም የፊሲካል ደህንነትን በማስጠበቅ የዜጎችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ስለመሆኑም ጠቅሰዋል።
በፕላንና ልማት ሚኒስቴር የልማት ዕቅድና የመንግሥት ኢንቨስትመንት አስተዳደር ሥራ አስፈጻሚ በረከት ፍስሃፅዮን÷የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ሙሉ ትግበራ በጠንካራ ሲቪል ሰርቪስ የገንዘብና የፊሲካል ፖሊሲ አቅምን በመገንባት የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ሥርዓትን ለማዘመን የሚያስችል መሆኑን አስረድተዋል።
በማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ትግበራው መንግሥት የነዳጅ፣ ማዳበሪያ፣ ዘይት፣ መድኃኒትና ሌሎችም ላይ ድጎማ ማድረጉ ጉልህ ፋይዳ ያለው መሆኑን አማካሪው አንስተዋል።
የግሉን ዘርፍ የውጭ ምንዛሬ ፍላጎት ምላሽ በመስጠት የተሻለ የምርታማነትና የግብዓት አቅርቦት እንዲኖር የሚያስችል መሆኑንም አቶ በረከት ተናግረዋል።
በፖሊሲ ትግበራው መነሻነት ከልማት አጋር ሀገራትና ተቋማት የሚገኝ የገንዘብ ድጋፍ በተሟላ መልኩ ለታለመለት ልማት ለማዋል ዝግጅት መደረጉን አንስተዋል።
ለተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ትግበራው ስኬታማነትም በተለይም ምሁራን፣ የፍትሕ ተቋማት፣ የንግዱ ማህበረሰብ አጠቃላይ ዜጎች የሚጠበቅባቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ማስገንዘባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።