አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢንዱስትሪውን ምርታማነት በማሳደግ የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማስፋት በትኩረት እየተሠራ መሆኑን የአማራ ክልል የኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ አስታወቀ፡፡
በ2017 በጀት ዓመት የክልሉን ኢኮኖሚ 15 ነጥብ 4 በመቶ ለመሸፈን እየተሠራ መሆኑንም ነው የቢሮው ኃላፊ እንድሪስ አብዱ የገለጹት፡፡
በክልሉ ተከስቶ በነበረው የፀጥታ ችግር ምክንያት ባለሃብቶች የማምረት ሥራቸውን እንዳያቋርጡ ጥረት መደረጉን፣ በጥሬ ዕቃና ሌሎች አቅርቦቶች እጥረትም አምራች ኢንዱስትሪዎች በ2015 ከነበሩበት 56 ነጥብ 4 በመቶ የማምረት አቅም በ2016 ወደ 54 በመቶ ዝቅ ማለቱን አብራርተዋል፡፡
ከ437 ቢሊየን ብር በላይ ያስመዘገቡ 2 ሺህ 650 አዳዲስ ባለሃብቶችን ወደ ክልሉ መሳብ መቻሉንም ጠቅሰዋል፡፡
በክልሉ የሚገኙ አምራች ኢንዱስትሪዎች ምርታቸውን ወደ ውጭ ልከው 149 ሚሊየን ዶላር መገኘቱን በመግለጽ÷የማኅበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ በተከናወነው ሥራ 44 ሺህ 102 ቋሚ የሥራ ዕድል ተፈጥሯል ብለዋል፡፡
በቀጣዩ የበጀት ዓመትም ጥራትና ውጤታማነትን በማስፈን፣ ቅንጅታዊ አሠራርን በማሻሻል ምርታማነትን ለማሳደግና የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማስፋት ትኩረት እንደሚደረግ አመላክተዋል፡፡
በደሳለኝ ቢራራ