የሀገር ውስጥ ዜና

በወላይታ ዞን የመሬት መንሸራተት አደጋ የተከሰተበት አካባቢ ነዋሪዎች ከስጋት ነፃ በሆነ አካባቢ ሰፈሩ

By Amele Demsew

August 06, 2024

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በወላይታ ዞን ካዎ ኮይሻ ወረዳ የመሬት መንሸራተት አደጋ የተከሰተበት ቀበሌ ነዋሪዎችን ከስጋት ነፃ ወደ ሆነ አካባቢ የማስፈር ስራ መከናወኑን የዞኑ የአደጋ ሥጋት ስራ አመራር ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ዳዊት ደሳለኝ እንደገለጹት÷ ትናንት በዞኑ ካዎ ኮይሻ ወረዳ ጤፓ ቀበሌ የተከሰተው የመሬት መንሸራተት አደጋ በሰውና ንብረት ላይ ጉዳት አድርሷል።

በቀበሌው ተጨማሪ አደጋ እንዳይከሰት የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸው÷ 57 አባወራዎችን ከስጋት ነፃ ወደ ሆነ አካባቢ የማስፈር ስራ ተሰርቷል ብለዋል።

በአደጋው ምክንያት የተፈናቀሉ ወገኖችን በጊዜያዊነት በትምህርት ቤቶች የማስጠለል ተግባራት በልዩ ትኩረት እየተከናወኑ መሆኑን መግለጻቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።

በዞኑ በሌሎች ወረዳዎችም ተመሳሳይ ችግር እንዳያጋጥም የጥንቃቄ መልዕክት የማስተላለፍና ነዋሪዎችን የማንቃት ተግባር እየተከናወኑ መሆኑንም አመልክተዋል።