Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

18 ቢሊየን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሀብቶች ፍቃድ ወስደው እንቅስቃሴ ጀምረዋል- ከንቲባ ከድር ጁሃር

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በድሬዳዋ 18 ቢሊየን ብር የሚጠጋ ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሀብቶች ፍቃድ ወስደው በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ እንቅስቃሴዎች መጀመራቸውን የአስተዳደሩ ከንቲባ ከድር ጁሃር ተናገሩ።

የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት 3ኛ ዙር 3ኛ የሥራ ዘመን 8ኛ መደበኛ ጉባዔ ከትናንት ጀምሮ እየተካሄደ ይገኛል።

በጉባዔው ላይ የአስፈፃሚውን የዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ያቀረቡት ከንቲባ ከድር ጁሃር÷በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 17 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ 95 ባለሃብቶች በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ለመሰማራት ፍቃድ ወስደው እንቅስቃሴ ጀምረዋል ብለዋል።

የኢንቨስትመንት ፍቃድ ወስደው እንቅስቃሴ የጀመሩት ባለሀብቶች ደግሞ ተኪ ምርቶችን በማምረት የውጭ ምንዛሬ የሚያስገኙ መሆናቸውን ነው የገለፁት።

በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄም በአስተዳደሩ ያሉትን የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶችን በመደገፍ እና በመከታተል ወደ ማምረት የተሸጋገሩ ኢንዱስትሪዎች ቁጥር እንዲጨምር አስችሏል ብለዋል።

በዚህም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ብቻ 5 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ 15 ኢንዱስትሪዎች ወደ ማምረት መሻገራቸውን ጠቅሰው፤ ከእነዚህ ውስጥ 11ዱ በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ የተሰማሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ወደ ማምረት የተሸጋገሩት አምራች ኢንዱስትሪዎች 4 ሺህ 250 ለሚሆኑ ሰዎች ቋሚ የስራ ዕድል መፍጠራቸውን ገልጸዋል።

እንደ ከንቲባ ከድር ገለፃ አገራዊውን ለውጥ ተከትሎ በተለይም በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በተካሄደው የተቀናጀ ድጋፍ እና ክትትል የተገኙ ውጤቶች ተጠናክረው ይቀጥላሉ።
በድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት 3ኛ ዙር 3ኛ ዓመት 8ኛ መደበኛ ጉባዔ የምክርቤቱ አባላት በከንቲባው ሪፖርት ላይ ውይይት ካደረጉ በኋላ በሙሉ ድምፅ ማፅደቃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

Exit mobile version