አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎ በምርቶች ላይ አላግባብ ዋጋ የሚጨምሩና የሚሰውሩ አካላትን የሚቆጣጠር ግብረ-ሃይል ተቋቁሞ ወደ ሥራ ገብቷል፡፡
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስዳድር አሻድሊ ሀሰን በሀገር አቀፍ ደረጃ መተግበር በጀመረው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ዙሪያ ከባለድርሻ ተቋማት አመራሮች ጋር ተወያይተዋል፡፡
አቶ አሻድሊ በዚህ ወቅት ÷ መንግስት እየተገበረ የሚገኘው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ የመጪውን ትውልድ ዘላቂ መብትና ጥቅም የሚያስከበር መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ለሀገር ዘላቂ ዕድገት ያለው ፋይዳ ታማኖበት ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎ አግባብነት የሌለው የዋጋ ጭማሪ እንዲሁም ምርት የመደበቅ ሁኔታዎች እየተስተዋሉ መሆኑን ጠቁመው÷መንግስት ይህንን ድርጊት ለመቆጣጠር ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሠራ ገልጸዋል፡፡
በክልሉ በምርቶች ላይ ያላግባብ ዋጋ የሚጨምሩ እና ምርት የሚሰውሩ አካላትን የሚቆጣጠር የተለያዩ የሚመለከታቸው ተቋማትን ያካተተ ግብረ-ሃይል ተቋቁሞ ወደ ሥራ መግባቱንም አስታውቀዋል፡፡
ህብረተሰቡ ምክንያታዊ ያልሆነ ዋጋ የሚጨምሩ እና ምርት የሚሰውሩ ስግብግብ ነጋዴዎችን ሲመለከተ ጥቆማ በመስጠት እንዲተባበር ጥሪ ማቅረባቸውንም የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡