የሀገር ውስጥ ዜና

በአማራ ክልል የኮሌራና የወባ በሽታዎችን ስርጭት ለመከላከልና ለመቆጣጠር ጥረት እየተደረገ ነው ተባለ

By Mikias Ayele

August 05, 2024

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል የኮሌራና የወባ በሽታዎችን የመከላከልና የመቆጣጠር ተግባር እየተከናወን መሆኑን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ያለፈው ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ግምግማና የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ የትውውቅ መድረክ በባህር ዳር ከተማ ተካሄዷል።

የቢሮ ኃላፊው አቶ አብዱልከሪም መንግስቱ እንደገለጹት÷በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በተደረገው የተቀናጀ ጥረት በዘርፉ አበረታች ስራ ማከናወን ተችሏል።

በተለይም የኮሌራና የወባ በሽታዎችን ለመከላከል መሰረታዊ የጤና አገልግሎቶችን ለህብረተሰቡ በማዳረስ  ለመቆጣጠር ጥረት መደረጉን አውስተዋል።

በተያዘው የበጀት ዓመትም የኮሌራ በሽታ ስርጭትን ለመግታት ህብረተሰቡ የግልና የአካባቢውን ንጽህና በመጠበቅ ራሱን ከበሽታው እንዲከላከል እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

እንዲሁም ለወባ በሽታ ተጋላጭ በሆኑ 22 ወረዳዎች ላይ የጸረ ወባ ኬሚካል ርጭት እየተከናወነ እንደሚገኝ ነው ያስረዱት፡፡

አሁንም ተጨማሪ ርጭት ለማከናወን ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ ጠቁመው÷ ህብረተሰቡ ለወባ በሽታ አጋላጭ የሆኑ ስፍራዎችን ማፅዳት እንዳለበት መልዕክት አስተላልፈዋል።

የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ጤና መምሪያ ሃላፊ አቶ ገበያው አሻግሬ በበኩላቸው÷በዞኑ የወባ በሽታን ለመከላከል 1 ነጥብ 3 ሚሊየን የአልጋ አጎበር በማሰራጨትና ህብረተሰቡን በማስተባባር የመከላከል ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛል ብለዋል።

በአሁኑ ወቅትም በዘጠኝ ወረዳዎች የጸረ ወባ ኬሚካል ርጭትና ህብረተሰቡ ከበሽታው መከላከል በሚቻልበት አግባብም ግንዛቤን የማስጨበጥ ስራ እየተከናወነ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡