አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዋሬ አካባቢ ለአቅመ ደካማ ወገኖች እየተከናወነ ያለው የቤት ግንባታ በታሰበው መሠረት እየሄደ መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አስታወቀ፡፡
በየዓመቱ ለአረጋውያን እና በኢኮኖሚ ዝቅተኛ ለሆኑ ወገኖች የሚደረገው የቤት እድሳት እና ግንባታ ላይ የሚያተኩረው ማኅበራዊ በጎ ሥራ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሥራዎች ቁልፍ ምሰሶ መሆኑን ጽሕፈት ቤቱ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ አስታውቋል፡፡
በዚህም በአዋሬ አካባቢ ለሰው የተሻለ እና የተከበረ አኗኗር ለመፍጠር እየተደረገ ያለው የለውጥ እንቅስቃሴ በፌደራል እና ክልል የመንግሥት አካላት የሚተገበረው የዚሁ ትልም ዐቢይ አካል ነው ተብሏል፡፡
የዘንድሮው ሥራም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በግንቦት ወር ማስጀመራቸውን ያስታወሰው ጽ/ቤቱ፥ ለአቅመ ደካማ ወገኖች የሚከናወነው የቤት ግንባታ በፍጥነት እየተከወነ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡