ዓለምአቀፋዊ ዜና

ብሊንከን ኢራንና ሂዝቦላህ በእስራኤል ላይ ጥቃት ሊሰነዝሩ እንደሚችሉ ተናገሩ

By Tamrat Bishaw

August 05, 2024

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ኢራንና ሂዝቦላህ በሚቀጥሉት 24 እና 48 ሰዓታት ውስጥ በእስራኤል ላይ ጥቃት ሊሰነዝሩ ይችላሉ ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

በመካከለኛው ምስራቅ ቀጣናዊ ጦርነት ሊቀሰቀስ ይችላል በሚል ከፍተኛ ስጋት መንገሱን የአሜሪካ ባለስልጣናትን መረጃዎች ጠቅሶ አልጀዚራ ዘግቧል፡፡

ባሳለፍነው ሳምንት ኢራንና ሂዝቦላህ የሃማስ እና የሂዝቦላህ ከፍተኛ መሪዎች ግድያን ተከትሎ አጸፋ እንደሚመልሱ መዛታቸው ይታወሳል።

ኢራን እና ሂዝቦላህ በእስራኤል ላይ ጥቃት ሊሰነዝሩ እንደሚችሉም ብሊንከን ለቡድን-7 አባል ሀገራት መናገራቸውን ዘገባው አመልክቷል፡፡

ጥቃቶቹ መቼ እና በምን አይነት ቅርፅ እንደሚወሰዱ ባይታወቅም÷ኢራንና ሂዝቦላህ አጸፋ እንደሚመልሱ አሜሪካ ታምናለች ነው ያሉት ሚኒስትሩ፡፡

ኢራን እና ሂዝቦላህ ጥቃት እንዳይሰነዝሩ እና ማንኛውም የእስራኤል ምላሽ እንዲገደብ አሜሪካ እንደምታሳምን ሚኒስትሩ መናገራቸው በዘገባው ተጠቅሷል፡፡

ሌሎች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችም በሦስቱ ሀገራት ላይ ዲፕሎማሲያዊ ጫና በመፍጠር ግፊቱን እንዲቀላቀሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በሌላ በኩል የእስራኤል ጦር በምዕራብ ገሊላ አካባቢ ከሊባኖስ የተተኮሱ ሮኬቶችና ሰው አልባ አውሮፕላኖችን ማክሸፉ ተነግሯል።

የአደጋ ማንቂያ ደውሎችም የከሸፉ ሮኬቶች እና ሚሳኤሎች ፍንጣቂዎች መውደቅን ተከትሎ ድምጽ ማሰማታቸውን ጦሩ በማህበራዊ ትስስር ገጹ አስታውቋል።