የሀገር ውስጥ ዜና

ክልሉ የነበሩ ችግሮችን በመቆጣጠር በአጭር ጊዜ የተረጋጋ ሁኔታ መፍጠሩ የሚደነቅ ነው – ወ/ሮ ሙፈሪሃት

By Melaku Gedif

August 05, 2024

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የነበሩ ችግሮችን በመቆጣጠር በአጭር ጊዜ በተደራጀ መንገድ የተረጋጋ ሁኔታ መፍጠሩ የሚደነቅ ነው ሲሉ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ገለጹ፡፡

የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ካቢኔ ጋር በሥራ ዕድል ፈጠራ ዘርፍ ጉዳዮች ዙሪያ እየመከረ ነው፡፡

ወ/ሮ ሙፈሪሃት÷ ክልሉ የነበሩ ውስብስብ ችግሮችን በመቆጣጠር በአጭር ጊዜ በተደራጀ መንገድ የተረጋጋ ሁኔታ ፈጥሮ ወደ ልማት መግባቱና አመርቂ ውጤት ማስመዝገቡ የሚደነቅ ነው ብለዋል፡፡

በሁሉም ዘርፍ የተጀመረው ጠንካራ እንቅስቃሴ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል።

ሚኒስቴሩ እንደ ግብ ባስቀመጣቸው የክህሎት ልማት፣ የስራ እድል ፈጠራ፣ የኢንዱስትሪ ሰላምና የተቋም ግንባታ ዙሪያ ከክልሉ ጋር በቅንጅት ለመስራት ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው በበኩላቸው÷ መድረኩ ክልሉና ሚኒስቴሩ በቅንጅት በሚሰሩበትና በዘርፉ ዙሪያ ለክልሉ በሚደረግ ድጋፍ ላይ ያተኮረ መሆኑን አንስተዋል፡፡

በውይይት መድረኩ ስለ ክልሉ አጠቃላይ ሁኔታ በርዕሰ መስተዳድሩ ልዩ አማካሪ አቶ ንጉሴ አስረስ ገለጻ መደረጉን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡