ስፓርት

ኢትዮጵያ በየትኛቹ ኦሊምፒኮች ተሳተፈች?

By ዮሐንስ ደርበው

August 05, 2024

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ዘንድሮ ለ15ኛ ጊዜ በኦሊምፒክ እየተሳተፈች የምትገኘው ኢትዮጵያ በታሪኳ በኦሊምፒክ መሳተፍ የጀመረችው ኦሊምፒክ ከተጀመረ ከ60 ዓመታት በኋላ አውስትራሊያ ባስተናገደችው 16ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ላይ ነው፡፡

በግሪክ አስተናጋጅነት በፈረንጆቹ 1986 የጀመረው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ውድድር አውስትራሊያ፣ ኦስትሪያ፣ ቡልጋሪያ፣ ቺሊ፣ ዴንማርክ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ በወቅቱ አጠራር ታላቋ ብሪታንያ (አየርላንድን ጨምሮ)፣ ግሪክ፣ ሀንጋሪ፣ ጣልያን፣ ስዊድን፣ ስዊዘርላንድና አሜሪካ ተሳትፈውበታል።

ኢትዮጵያ በመጀመሪያ ተሳትፎዋ በማራቶን፣ ዱላ ቅብብል እና ብስክሌት ስፖርቶች ተካፍላ ሜዳሊያ ባለማግኘቷ ደረጃ ውስጥ ሳትገባ ቀርታለች፡፡

ሁለተኛ ተሳትፎዋ በሆነው በፈረንጆቹ 1960 ጣልያን ባስተናገደችው 17ኛው ኦሊምፒክም በአትሌቲክስና ብስክሌት የስፖርት ዓይነቶች ተሳትፋ፤ አትሌት አበበ ቢቂላ ባስገኘው የወርቅ ሜዳሊያ 21ኛ ደረጃን በመያዝ ውድድሩን አጠናቅቃለች።

ጃፓን በፈረንጆቹ 1964 ባሰናዳችው 18ኛው ኦሊምፒክ በአትሌቲክስ፣ ቦክስና ብስክሌት ስፖርቶች የተሳተፈችው ኢትዮጵያ÷ በአትሌት አበበ ቢቂላ የወርቅ ሜዳሊያ 24ኛ ደረጃን ይዛ ጨርሳለች።

19ኛው ኦሊምፒክ በፈረንጆቹ 1968 በሜክሲኮ ሲካሄድ በአትሌቲክስ፣ ቦክስና ብስክሌት የስፖርት ዓይነቶች ተሳትፋ÷ አትሌት ማሞ ወልዴ በማራቶን ወርቅ፣ በ10 ሺህ ሜትር ደግሞ ብር ሜዳሊያ በማምጣቱ 25ኛ ደረጃን ይዛ ማጠናቀቋ ይታወሳል፡፡

ጀርመን በፈረንጆቹ 1972 ባስተናገደችው 20ኛው የኦሊምፒክ ውድድር በአትሌቲክስ፣ ቦክስ እና ብስክሌት ተሳትፋ÷ አትሌት ማሞ ወልዴ በማራቶን እንዲሁም ምሩጽ ይፍጠር በ10 ሺህ ሜትር ባመጡት የነሐስ ሜዳሊያ ኢትዮጵያ 41ኛ ደረጃን ይዛ ጨርሳለች።

በፈረንጆቹ 1980 ሩሲያ ባስተናገደችው 22ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ደግሞ ኢትዮጵያ በአትሌቲክስ፣ ቦክስና ብስክሌት ስፖርቶች ተሳትፋ÷ ማርሽ ቀያሪው አትሌት ምሩጽ ይፍጠር በ5 ሺህ እና 10 ሺህ ሜትር ውድድሮች ሁለት የወርቅ ሜዳሊያዎችን አስገኝቶላታል፡፡

በፈረንጆቹ 1992 ስፔን ባዘጋጀችው 25ኛው የኦሊምፒክ ውድድር ኢትዮጵያ በአትሌቲክስ እና ብስክሌት ተካፍላ÷ በአትሌት ደራርቱ ቱሉ 10 ሺህ ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ፣ አዲስ አበበ በ10 ሺህ ሜትር ወንዶች እና ፊጣ ባይሳ በ5 ሺህ ሜትር ወንዶች የነሐስ ሜዳሊያዎች በማግኘት 33ኛ ደረጃን ይዛ አጠናቅቃለች።

እንዲሁም 26ኛው የኦሊምፒክ ውድድር በአሜሪካ ሲካሄድ በአትሌቲክስና ቦክስ ስፖርቶች የተሳተፈችው ኢትዮጵያ በአትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ በ10 ሺህ ሜትር ወርቅ፣ ፋጡማ ሮባ በማራቶን ወርቅ፣ ጌጤ ዋሚ በ10 ሺህ ሜትር ነሐስ ሜዳሊያዎችን አግኝታ 34ኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።

አውስትራሊያ ያዘጋጀችው 27ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች በፈረንጆቹ 2000 ሲካሄድ ኢትዮጵያ በአትሌቲክስና ቦክስ ተሳትፋ ደማቅ ታሪክ ማስመዝገቧ ይታወቃል፡፡

በዚህ ኦሊምፒክ አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ በ10 ሺህ ሜትር ወርቅ፣ ደራርቱ ቱሉ በ10 ሺህ ሜትር ወርቅ፣ ሚሊዮን ወልዴ በ5 ሺህ ሜትር ወርቅ፣ ገዛኸኝ አበራ በማራቶን ወርቅ፣ ጌጤ ዋሚ በ10 ሺህ ሜትር ብርና በ5 ሺህ ሜትር ነሐስ፣ አሰፋ መዝገቡ በ10 ሺህ ሜትር እና ተስፋዬ ቶላ በወንዶች ማራቶን በተመሳሳይ የነሐስ ሜዳሊያዎችን አግኝተው ኢትዮጵያ በውድድሩ 8 ሜዳሊያዎችን በማግኘት 20ኛ ደረጃን ይዛ ጨርሳለች።

ግሪክ በፈረንጆቹ 2004 ባስተናገደችው 28ኛው ኦሊምፒክም ኢትዮጵያ በአትሌቲክስና ቦክስ ተሳትፋ አትሌት ቀነኒሳ በቀለ በ10 ሺህ ሜትር ወርቅ እና በ5 ሺህ ሜትር ብር፣ መሰረት ደፋር በ5ሺህ ወርቅ፣ በ10 ሺህ ሜትር እጅጋየሁ ዲባባ የብር፣ ስለሺ ስኅን በ10 ሺህ ብር፣ አትሌት ደራርቱ ቱሉና ጥሩነሽ ዲባባ ነሐስ ሜዳሊያ አግኝተው በ7 ሜዳሊያዎች 28ኛ ደረጃን በመያዝ ውድድሩን ማጠናቀቅ ችላለች፡፡

29ኛውን የኦሊምፒክ ውድድር በ2008 ቻይና ባስተናገደችበት ወቅትም በአትሌቲክስ ስፖርት ብቻ የተሳተፈችው ኢትዮጵያ በአትሌት ቀነኒሳ በቀለና ጥሩነሽ ዲባባ በ5 ሺህ እና 10 ሺህ ሜትር ወርቅ፣ ስለሺ ስኅን በ10 ሺህ ሜትር ብር እና መሰረት ደፋር ብር ሜዳሊያዎችን በማግኘት ከ204 ሀገራት 18ኛ ደረጃን ይዛ አጠናቅቃለች፡፡

በ2012 ብሪታንያ 30ኛውን ኦሊምፒክ ስታዘጋጅ 12ኛ ተሳትፎዋን ያደረገችው ኢትዮጵያ በአትሌቲክስና ውኃ ዋና ስፖርቶች ተካፍላ በአትሌት ጥሩነሽ ዲባባ በ10 ሺህ ሜትር ወርቅ እና በ5 ሺህ ሜትር ነሐስ፣ መሰረት ደፋር 5 ሺህ ሜትር ወርቅ፣ ቲኪ ገላና በማራቶን ወርቅ፣ ደጀን ገብረ መስቀል በ5 ሺህ ሜትር ብር፣ ሶፊያ አሰፋ በ3 ሺህ ሜትር መሰናክል ብር፣ ታሪኩ በቀለ በ10 ሺህ ሜትር እና አበባ አረጋዊ በ1 ሺህ 500 ሜትር ነሐስ ሜዳሊያዎችን አግኝተው ኢትዮጵያ በ8 ሜዳሊያዎች 24ኛ ደረጃን ይዛ ማጠናቀቋ ይታወሳል፡፡

በፈረንጆቹ 2016 በብራዚል በተካሄደው 31ኛው የኦሊምፒክ ውድድር በአትሌቲክስ፣ ብስክሌትና ውሃ ዋና ስፖርቶች በመሳተፍ በአትሌት አልማዝ አያና በ10 ሺህ ሜትር ወርቅ እና በ5 ሺህ ሜትር ነሐስ፣ ፈይሳ ሌሊሳ በማራቶን ብር፣ ገንዘቤ ዲባባ በ1 ሺህ 500 ሜትር ብር፣ ታምራት ቶላ በ10 ሺህ ሜትር፣ አትሌት ሐጎስ ገብረ ሕይወት በ5 ሺህ ሜትር፣ ጥሩነሽ ዲባባ በ10 ሺህ ሜትር እና ማሬ ዲባባ በማራቶን በተመሳሳይ የነሐስ ሜዳሊያ በማግኘት ኢትዮጵያ 8 ሜዳሊያዎችን በማግኘት 44ኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።

ጃፓን 32ኛውን የኦሊምፒክ ውድድር ስታስተናግድ ኢትዮጵያ በአትሌቲክስ፣ ብስክሌት፣ ውሃ ዋና እንዲሁም በቴኳንዶ ተሳትፋ በውድድሩ አትሌት ሰለሞን ባረጋ በ10 ሺህ ሜትር ወንዶች ወርቅ፣ ለሜቻ ግርማ በ3 ሺህ ሜትር መሰናክል ብር፣ ጉዳፍ ፀጋይ በ5 ሺህ ሜትር እና ለተሰንበት ግደይ በ10 ሺህ ሜትር በተመሳሳይ የነሐስ ሜዳሊያ አምጥተው በ4 ሜዳሊያዎች 56ኛ ደረጃን በመያዝ በኦሊምፒክ ተሳትፎዋ ታሪክ ዝቅተኛውን ውጤት አስመዝግባለች።

ካናዳ በፈረንጆቹ 1976 ባስተናገደችው 21ኛው ኦሊምፒክ፣ አሜሪካ በ1984 ባዘጋጀችው 23ኛው ኦሊምፒክ እና ደቡብ ኮሪያ በ1988 ባስተናገደችው 24ኛው የኦሊምፒክ ውድድሮች ኢትዮጵያ አልተሳተፈችም፡፡

ዘንድሮ በፈረንሳይ አስተናጋጅነት 33ኛው የኦሊምፒክ ውድድር እየተካሄደ ሲሆን ኢትዮጵያ 15ኛ በሆነው ተሳትፎዋ በአትሌቲክስና ውሃ ዋና ስፖርቶች 38 ስፖርተኞችን እያሳተፈች ሲሆን እስካሁን በ10 ሺህ ሜትር ወንዶች በአትሌት በሪሁ አረጋዊ አማካኝነት የብር ሜዳሊያ አግኝታለች።

መልካም ዕድል ለኢትዮጵያ!!