ዓለምአቀፋዊ ዜና

የእስራኤል ጦር በኢራን የሚፈጸምን ጥቃት ለመመከት በተጠንቀቅ ላይ መሆኑን አስታወቀ

By Melaku Gedif

August 04, 2024

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 28፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የእስራኤል ጦር ኢራን እፈጽመዋለሁ ላለችው ጥቃት አስፈላጊውን ምላሽ ለመስጠት በተጠንቀቅ ላይ መሆኑን አስታውቋል፡፡

በቅርቡ የሃማስ ከፍተኛ የፖለቲካ ሃላፊ ኢስማኤል ሃኒዬህ እና የሊባኖስ ታጣቂ ቡድን ሂዝቦላ ከፍተኛ አዛዥ በኢራን መገደላቸው ይታወሳል፡፡

ኢራን ለግድያው እስራኤልን ተጠያቂ ያደረገች ሲሆን÷በአንጻሩ እስራኤል በጉዳዩ ላይ ምላሽ ከመስጠት ተቆጥባለች፡፡

ድርጊቱን ተከትሎም ኢራን በእስራኤል ላይ ከባድ አጸፋዊ እርምጃ እወስዳለሁ ስትል በተደጋጋሚ አስጠንቅቃለች፡፡

ከነገው ዕለት ጀምሮ ሊፈጸም ይችላል በተባለው መጠነ ሰፊ ጥቃት የሂዝቦላ ታጣቂ ቡድን ሊሳተፍ እንደሚችል ተመላክቷል፡፡

እስራኤል በበኩሏ÷ከኢራን ሊፈጽም የሚችልን ማንኛውንም ጥቃት ለመመከት ከአሜሪካ ጋር አስተማማኝ ዝግጅት እያደረገች መሆኑን አስታውቃለች፡፡

ከጉዳዩ ጋር ተያይዞም የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ ሃላፊ ሚካኤል ኩሪላ እስራኤል መግባታቸው ነው የተገለጸው፡፡

በመካከለኛው ምስራቅ ውጥረት መንገሱን ተከትሎ አሜሪካ እስራኤልን ለመከላከል ቁርጠኛ መሆኗን ያረጋገጠች ሲሆን÷ለዚህም የሚሳኤል መከላከያ በቀጣናው ለማሰማራት ዝግጁ መሆኗን ገልጻለች፡፡

የእስራኤል ጦርም ለጥቃቱ አስፈላጊውን ምላሽ ለመስጠት በከፍተኛ ተጠንቀቅ ላይ እንዲቆም ትዕዛዝ መሰጠቱን አር ቲ ዘግቧል፡፡