አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 28፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ለ25 ሺህ ዜጎች ነጻ የሕክምና ምርመራ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል የክረምት የጤና በጎ ፈቃድ አገልግሎት ተጀምሯል፡፡
የጤና ሚኒስቴር እና ተጠሪ ተቋማት አመራርና ሠራተኞች በአሶሳ ከተማ ተገኝተው የክረምትበጎ ፈቃድ ሥራ አስጀምረዋል፡፡
የበጎ ፍቃድ አገልግሎቱ በደም ልገሳ፣ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ነፃ ምርመራ፣ የቤት እድሳት እና በአረንጓዴ አሻራ እንደሚተገበር የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ ተናግረዋል።
የጤና ሚኒስቴር እና ተጠሪ ተቋማት ከፍተኛ የአመራር አባላቱ የአሶሳ አጠቃላይ ሆስፒታል የአገልግሎት አሰጣት ሒደትንም ጎብኝተዋል።
ሚኒስቴሩ በክልሉ የጤና ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ እንዲሻሻል ድጋፍ እንደሚያደርግ ዶ/ር መቅደስ ገልጸዋል።
ይህንን አብነት ወስዶ ሌሎቹም የበጎ ፈቃድ ሥራውን ማጠናከር እንዳለባቸው ያስታወቁት ሚኒስትሯ÷ በተለይም የክረምቱ ወራት ለሰዎች አለን የምንልበትና በጎ ነገር የምንሰራበት መሆን አለበት ብለዋል።
የአመራር አባላቱ በክልሉ የቤተሙከራ እና የምርምር ማዕከል ግንባታንየጎበኙ ሲሆን÷የማዕከሉ ግንባታ 65 በመቶ መድረሱና በቀጣይ 8 ወራት ውስጥ እንደሚጠናቀቅ መገለጹን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡
የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻዲሊ ሃሰን ሚንስቴሩ ባለፉት ዓመታት የጤና ተቋማትን መልሶ ለማደራጀት ላደረገው ድጋፍ አመስግነዋል።
የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ወልተጂ በጋሎ በበኩላቸው÷ የተጀመረውን የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ለማስቀጠል ዝግጁ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎቹ በአሶሳ አጠቃላይ ሆስፒታል የድንገተኛ ህክምና መስጫ ማዕከል ግንባታ የመሰረት ድንጋይ ያስቀመጡ ሲሆን÷ በሆስፒታሉ የችግኝ ተከላ አካሂደዋል።