አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ቀበሌ በተከሰተው የመሬት መንሸራተት ምክንያት የተጎዱ ሰዎችን ከአደጋ ለመከላከልና በዘላቂነት ችግሩ ለመፍታት በአዲስ መልክ ተፈናቃዮች ለማስፈር የቦታ ቅየሳ ሥራ እየተሠራ መሆኑ ተገልጿል።
በክልሉ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የዲላ ክላስተር አስተባባሪ እና የውሃና ማዕድን ቢሮ ኃላፊ አክሊሉ አዳኝ (ኢ/ር) የተመራው ልዑክ የኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ ተፈናቃዮችን በዘላቂነት ቡርዳ በሚባልበት ስፍራ ለማስፈር እየሠራ ነው ተብሏል።
በገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ በመሬት መንሸራተት ምክንያት ለተፈናቀሉ ወገኖች መልሶ የሚያሰፍርና የማቋቋም ኮሚቴ የቦታ ቅየሳ ሥራ እያካሄደ እንደሚገኝ ከርዕሰ መስተዳድር ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ስራው ሲጠናቀቅ 117 ሄክታር መሬት ላይ በመጀመሪያ ዙር 627 አባዎራዎችና እማዎራዎች እንደሚሰፍሩም ተመላክቷል።
በተመረጠው የመልሶ ማስፈሪያ ቦታ የባለሙያ ቡድን በመገኘት ለንድፍ ሥራና ለማህበራዊ ምጣኔ ሀብት መረጃ የሚረዱ መረጃዎችን የመሰብሰብ ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝም ተጠቁሟል።