Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያን ተከትሎ ህገ ወጥ ስራን እየሰሩ በሚገኙ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ እየተወሰደ ነው

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያን ተከትሎ ህገ ወጥ ስራን እየሰሩ በሚገኙ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ እየተወሰደ እንደሚገኝ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ሚኒስቴሩ ከክልልና ከከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ ጋር በጋራ በመሆን በሀገሪቱ የተደረገውን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያን ተከትሎ ህገ ወጥ ስራን እየሰሩ በሚገኙ ነጋዴዎች ላይ እርምጃዎችን እየወሰድኩ እገኛለሁ ብሏል፡፡

ከብሔራዊ የንግድ ተቋማት የፀረ ህገ ወጥ ንግድና ገበያ መቆጣጠርያ የጋራ ኮሚቴ አባላት ጋር የህገ ወጥ የሸቀጦች ዋጋ ጭማሪና ምርትን የማከማቸት ህገ ወጥ ተግባርት ዙሪያ በየክልሉ እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች አፈፃፀምን መገምገማቸውን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትሩ ካሳሁን ጎፌ(ዶ/ር) ገልጸዋል።

በሪፖርቱ አበረታች የሆነ ጅምር የህገ ወጥ ንግድ ቁጥጥር ተግባራት እየተከናወኑ እንደሚገኙ ገልጸው ፥ በሚቀጥሉት ቀናትም ቁጥጥሩ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ማሳሰባቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ለአብነት በዛሬው ቀን ብቻ ያለአግባብ ዋጋ በጨመሩ፣ ምርት በደበቁና ለህግ ተገዢ ባልሆኑ 967 የንግድ ተቋማት የማሸግ እርምጃ ሲወሰድ ዘጠኙ ደግሞ የንግድ ፈቃድ እገዳ ተጥሎባቸዋል ፤ በተመሳሳይ የሁለት ተቋማት ፈቃድ ተሰርዟል ነው የተባለው፡፡

ከህገ ወጥ ተግባራቸው እንዲታረሙና ማስተካያ እንዲያደርጉ ተነግሯቸው ለማስተካከል ፍቃደኛ ያልሆኑ 49 ነጋዴዎች በእስራት መቀጣታቸውንም ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

በአጠቃላይ እስከዛሬ ድረስ 2ሺህ202 የንግድ ተቋማት ላይ የማሸግ እርምጃ ሲወሰድ፤ በ18ቱ ላይ የንግድ ፍቃድ እገዳ እንዲሁም በሥድስት ተቋማት ላይ የንግድ ፍቃድ ስረዛ እርምጃዎች ሲወሰዱ ከህገ ወጥ ተግባራቸው ለመታረም ፍቃደኛ ባልሆኑ 87 ነጋዴዎች ላይ የእስራት ቅጣት ተጥሏል ተብሏል፡፡

Exit mobile version