የሀገር ውስጥ ዜና

የክልሉ የኮሪደር ልማት ስራ የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ትኩረት አድርጎ እየተሰራ ነው – አቶ ኦርዲን በድሪ

By Meseret Awoke

August 03, 2024

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 27፣ 2016(ኤፍ ቢ ሲ) በሐረሪ ክልል እየተተገበረ በሚገኘው የኮሪደር ልማት ስራ የማህበረሰቡን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት በሚያረጋገጥ መልኩ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ እንደሚገኝ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ገለፁ።

የሐረር ከተማ ስትራቴጂክ የልማት እቅድ ግብረ-ሃይል በሐረር ከተማ እየተተገበሩ የሚገኙ የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶችን ተዘዋውሮ ተመልክቷል።

በከተማው እየተከናወኑ የሚገኙ የኮሪደር ልማት፣ የከተማ ፅዳትና ውበት እንዲሁም የኢንቨስትመንት ስራዎች በእለቱ ምልከታ ከተደረገባቸው ፕሮጀክቶች ውስጥ ይገኙበታል።

ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ በመስክ ምልከታው ወቅት እንዳሉት ፥ በክልሉ በመልሶ ልማት፣ በከተማ ፅዳትና ውበት እንዲሁም በኮሪደር ልማት ዘርፍ ውጤታማ ተግባራት እየተከናወኑ ነው።

በተለይ በፅዳትና ውበት የእግረኛ መንገዶችን ለዜጎች ምቹ እንዲሆን ለማስቻል የተሰጠው ትኩረት የከተማዋን እድገት በማፋጠን ረገድ ያለው አስተዋፅኦ የላቀ መሆኑንም ነው የተናገሩት።

በክልሉ ተግባራዊ እየተደረገ በሚገኘው የኮሪደር ልማት የአካባቢን ገፅታ ከመቀየር ባሻገር በልማት ስራው የማህበረሰቡን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት በሚያረጋገጥ መልኩ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

እየተከናወኑ የሚገኙ ሁሉን አቀፍ የልማት ስራዎችን ከማስቀጠል ጎን ለጎን ጠንካራ አደረጃጀት በመፍጠር ከተማው በፕላንና በስርዓት እንዲመራ የማድረግ ተግባርም በላቀ ትኩረትና ቁርጠኝነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አመላክተዋል።

በክልሉ በከተማ ልማት ዘርፍ እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባራት ከተማዋና ህዝቡን የሚመጥኑ በተለይ ከነዋሪው ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸው መሆናቸውንም አንስተዋል።

በሌላ በኩል በሂደት ላይ የሚገኙ የልማት ስራዎችን በተሻለ ፍጥነት በማጠናቀቅ በአዲሱ 2017 በጀት ዓመት ለማከናወን በዕቅድ የተያዙ ስራዎች ላይ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ አቅጣጫ አስቀምጠዋል።

በመሆኑም እየተሰሩ በሚገኙ የልማት ስራዎችም ማህበረሰቡን በባለቤትነት በማሳተፍ አጠናክሮ ማስቀጠል ወሳኝ መሆኑን መናገራቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።