Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የኢትዮጵያ ሴቶች እግር ኳስ ሽልማት ተከናወነ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የ2016 የውድድር ዘመን የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ እና የኢትዮጵያ ሴቶች ከፍተኛ ሊግ ውድድር የእውቅና ሥነ-ስርዓት ተከናውኗል፡፡

በመርሐ-ግብሩ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት እና የካፍ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል አቶ ኢሳያስ ጅራ፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ባሕሩ ጥላሁን፣ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት፣ የውድድር ኮሚቴ አመራሮች፣ ዕጩዎች እና ተሸላሚዎች፣ የሚዲያ አካላት እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡

የ2016 የውድድር ዘመን የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ኮከብ ተጫዋች፣ ኮከብ አሰልጣኝ፣ ኮከብ ግብ ጠባቂና ኮከብ ጎል አስቆጣሪዎች የእውቅና አሰጣጥ መርሐ-ግብር ተከናውኗል።

የ2016 የውድድር ዘመን የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ሲሳይ ገ/ዋህድ ከኢትዮ-ኤሌክትሪክ በኮከብ ተጫዋችነት፣ ብርሃኑ ግዛው ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኮከብ አሰልጣኝነት፣ አበባ አጄቦ ከአዲስ አበባ ከተማ በኮከብ ግብ ጠባቂ እና ሴናፍ ዋቁማ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኮከብ ጎል አስቆጣሪ እውቅና ተሰጥቷቸዋል፡፡

እንዲሁም የውድድር ዘመኑ ምርጥ ግብ ጠባቂ፣ ተከላካዮች፣ አማካዮችና አጥቂዎችም እውቅና እንደተሰጣቸው ከፌዴሬሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ከኢትዮጵያ ሴቶች ከፍተኛ ሊግም በተመሳሳይ ድርሻዬ መሐመድ ከቂርቆስ ክ/ከተማ በኮከብ ተጫዋችነት ፣ ልዩወርቅ መንበረ ከባህርዳር ከተማ በኮከብ ግብ ጠባቂ፣ ቤተልሔም ሽመልስ ከፋሲል ከነማ በኮከብ ጎል አስቆጣሪ እውቅና ተሰጥቷቸዋል፡፡

እንዲሁም እንዳልካቸው ጫካ ከቂርቆስ ክፍለ ከተማ በኮከብ አሰልጣኝነት ዕውቅና እንዳገኙ መረጃው ያመላክታል፡፡

በሴቶች ከፍተኛ ሊግ የ2016 የውድድር ዘመን ምርጥ 11 ግብ ጠባቂ፣ ተከላካዮች፣ አማካዮች እና አጥቂዎች ዕውቅና ተሰጥቷቸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሴቶች እግር ኳስ የ2016 የውድድር ዘመን ምስጉን የጨዋታ አመራሮች÷ ምስጉን ዋና እና ረዳት ዳኞችም እውቅና ተሰጥቷቸዋል፡፡

Exit mobile version