አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ እና የተለያዩ ሚኒስትሮች የነጌሌ ቦረናን አየር ማረፊያ የስራ ሂደት ጎብኝተዋል፡፡
አየር ማረፊያው በ1 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ወጭ እየተገነባ የሚገኝ ሲሆን ፥ በቀጣይ ዓመት አጋማሽ የሚጠናቀቅ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ በዚህ ወቅት ፥ አካባቢው የኢትዮጵያ ብልፅግና ለማረጋገጥ የሚያስችል ሰፊ አቅም በሁሉም መስክ ያለው ነው ብለዋል፡፡
ይህን አቅም ለመጠቀም አየር መንገዱ ትልቅ አስተዋፅኦ ያለው መሆኑንም ነው ያነሱት።
አቶ ሽመልስ አክለውም ፥ ይስተዋሉ የነበሩ የገበያ ትስስር ችግሮችን ይፈታል ፤ በአካባቢው ላለው ሃብት የማዕከላዊ እንዲሁም ዓለም ዓቀፍ የገበያ ዕድሎችን ያሰፋል ብለዋል።
በተመሳሳይ ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ እና ሚኒስትሮቹ በምስራቅ ጉጂ ዞን የተለያዩ የልማት ስራዎችን ጎብኝተዋል፡፡
በጉብኝቱ ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳን ጨምሮ በብልፅግና ፓርቲ የኦሮሚያ ቅርንጫፍ ፅ/ቤት ኃላፊ ፍቃዱ ተሰማ፣ የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ፣ የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስትር አለሙ ስሜና ሌሎችም የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
በመራዖል ከድር