በዚህም መሰረት የኢትዮጵያ አየር መንገድ አመራሮችና ሠራተኞች በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባ ቦሌ ክፍለ ከተማ በተለምዶው አየር መንገድ ጀርባ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር አከናውነዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ጣሰው በወቅቱ እንደገለጹት፤ አየር መንገዱ 40 ሄክታር በሚሆን ስፍራ ላይ 16 ዓይነት ሀገር በቀል የሆኑ 50 ሺህ ችግኞች ለመትከል አቅዶ እስካሁን 27 ሺህ ያህል ችግኞች ተክሏል።
በተመሳሳይም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዋናው መ/ቤት፣ አራዳ፣ የካና መገናኛ ዲስትሪክት የሥራ ሃላፊዎችና ሠራተኞች በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፖርክ ውስጥ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በማካሄድ አረንጓዴ አሻራቸውን አኑረዋል።
በመርሐ ግብሩ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት ተወካይ አቶ ኤፍሬም መኩሪያ ባንኩ ባለፉት ዓመታት በገፈርሳ፣ በሰበታ፣ በቢሾፍቱ፣ በጣሊያን ምሽግ፣ በእንጦጦ ተራራ፣ በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ፣ እንዲሁም በአይሲቲ ፓርክ ችግኝ መትከሉን አስታውሰዋል።
የሚተከሉ ችግኞችን ተንከባክቦ ለውጤት እንዲበቁ ባንኩ ሃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮ ኢንጅነገሪንግ ግሩፕ እና በስሩ የሚገኙ ፋብሪካዎች በዛሬው ዕለት በአቃቂ ቤዚክ ሜታልስ ኢንዱስትሪ ተገኝተው ችግኝ በመትከል አረንጓዴ አሻራቸውን አኑረዋል።
የኢትዮ ኢንጅነሪንግ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ አምባሳደር ሱሌማን ደደፎ፤ ተቋሙ ከዚህ ቀደም በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር መሳተፉን አስታውሰው፤ በዘንድሮ ክረምት እስከ 20 ሺህ ችግኞችን ለመትከል መታቀዱን ገልጸዋል።
ኢንዱስትሪዎች በአግባቡ ካልተያዙ ለተፈጥሮ ሚዛን መዛባት ትልቅ ጉዳት ያደርሳሉ በማለት ገልጸው፤ ኢንዱስትሪዎቻችን ተፈጥሮ ላይ ጥቃት የማይፈጽሙ እንዲሆኑ ተፈጥሮን መጠበቅ አለብን ብለዋል።