የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ በተመለከተ ማብራሪያ የሰጡት አቶ ማሞ ምህረቱ፤ ከሀገራዊ ለውጡ በፊት የነበረው የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ኢትዮጵያን ለውጭ ምንዛሬ እጥረት የዳረገ፣ የግል ሴክተሩን ከብድር ያገለል እና ከፍተኛ የብድር ጫና እንደነበረበት አስታውሰዋል።
ከለውጡ በፊት የነበረው ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የመንግስት ኢንቨስትመንትን መሰረት ያደረገ በመሆኑ ፋይናንስ የተደረገበት መንገድ ጤናማ እንዳልነበርም አውስተው፤ በዚህም የለውጡ መንግስት ሀገር በቀል ኢኮኖሚ ሪፎርም በመንደፍ የማክሮ ኢኮኖሚ ስብራትን ለመጠገን የሚያስችሉ እርምጃዎችን መውሰዱን ተናግረዋል።
በዚህም በመጀመሪያው ሀገር በቀል ኢኮኖሚ ሪፎርም ትግበራ ውስጣዊና ውጫዊ ተጽእኖዎችን በመቋቋም ትልቅ ውጤት ማስመዝገቡን ገልጸዋል።
ለአብነትም ኢትዮጵያ የነበረባትን የብድር ጫና ከ40 በመቶ ወደ 17 ነጥብ 4 በመቶ እንዲቀንስ መደረጉን ጠቁመው፤ የፋይናንስ ተቋማት ከሚሰጡት ብድር 88 በመቶውን ለግሉ ሴክተር ተደራሽ ማድረጋቸውን ነው ያነሱት፡፡
በተመሳሳይ አዳዲስ የኢንቨስትመንት ዘርፎች እንዲከፈቱ፤ የመንግስት የልማት ድርጅቶች በስርዓት እንዲመሩ እንዲሁም የኢኮኖሚ ስብራቱን መጠገንን መሰረት ያደረጉ አዳዲስ ተቋማት እንዲደራጁ መደረጉን ገልጸዋል፡፡
ይህን ስኬት በማስቀጠል ህዝብን ተጠቃሚ ለማድረግም ወደ ተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ትግበራ መገባቱን ገልጸዋል።
የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሙ ከመንግስት ዕቅዶችና ፖሊሲዎች ጋር የተጣጣመ መሆኑን ገልጸው፤ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ እድገትና ብልጽግና በጽኑ መሰረት ላይ የሚያቆምና ህዝቡን ተጠቃሚ የሚያደረግ እንደሆነም አጽኖት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡
ለአብነትም ሪፎርም የገቢ አስተዳደርና አሰባሰብ፣ የገንዘብ እንዲሁም የውጭ ምንዛሪ አስተዳደርን ጨምሮ ሁሉንም ዘርፎች በማስተሳሰር የሚተገበር መሆኑን አንስተው፤ የውጭ ምንዛሪ ችግርን በዘላቂነት የሚፈታ ቁልፍ ውሳኔ ስለመሆኑም አብራርተዋል፡፡
በማክሮ ኢኮኖሚው ስብራት የሚጠገነውና ኢኮኖሚ ዕድገቱ የሚቀጥለው ሪፎርሙ ወደ ተሟላ ትግበራ ሲገባ ብቻ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡
የሪፎርሙ ትግበራ ቀጣይነት ያለው ጤናማ የኢኮኖሚ ዕድገት እንዲኖር የሚያደርግ መሆኑን ገልጸው፤ በዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) ትንበያ ብቻ በቀጣይ አራት ዓመታት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በአማካይ 8 በመቶ ያድጋል ብለዋል፡፡
በዚህም ሪፎርሙ በገቢ ማሰባሰብ አቅም የሚፈጥር፣ የውጭ ምንዛሪ ክምችት የሚጨምር፣ ኤክስፖርትና ኢንቨስትመንትን ትርጉም ባለው መልኩ የሚለውጥ እንዲሁም የኢኮኖሚ ፍትሃዊነትን የሚያሰፍን እንደሆነ ጠቁመዋል።
ብሔራዊ ባንክ ካደረጋቸው ሪፎርሞች መካከል የውጭ ምንዛሬ ስርዓቱ መቀየር አንዱ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከሰሞኑ ይፋ የተደረገው የውጭ ምንዛሬ አስተዳደር ሕግ ማዕቀፍም በርካታ ለውጦች የሚያመጣ እንደሆነ ገልጸዋል።
ለአብነትም በብሔራዊ ባንክ ብቻ ይተመን የነበረው ስርዓት በመደበኛና እና በትይዩ ገበያ የተራራቀ ልዩነትን ማስፋትን ጨምሮ በርካታ ችግሮች እንደነበሩበት ጠቅሰው፤ ከዚህ አኳያ የውጭ ምንዛሬ ተመን በገበያው እንዲወሰን መደረጉን ገልጸዋል።
የምንዛሬ ተመኑ በገበያ መወሰኑ ሕገ ወጥነትና ብልሹ አሰራርን በመቅረፍ ኤክስፖርትና ኢንቨስትመንት ለማበረታታት ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት ማብራራታቸውን የዘገበው ኢዜ ነው።
ይህም የውጭ ምንዛሬ ስርዓቱ የተረጋጋና ጤናማ እንዲሆን ያደርጋል ያሉት ማሞ ምህረቱ፤ በዚህ ሂደት የገበያ ስርዓቱ ችግር ካጋጠው ብሔራዊ ባንክ ጣልቃ ገብቶ እንደሚያስተካከልም አስገንዝበዋል።
የፖሊሲ ለውጡ የ10 ዓመት መሪ የልማት እቅድን መሰረት አድርጎ ተግባራዊ መደረጉን ጠቅሰው፤ ይህም አሁን ያልተጀመረና ከ5 ዓመታት በፊት ጀምሮ ምክክር ሲደረግበት የቆየ አጃንዳ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ሪፎርሙ በየትኛውም ወገን ጣልቃ ገብነትና ጫና ሳይሆን የኢትዮጵያን ጥቅም መሰረት አድርጎ የተከናወነ መሆኑን አንስተው፤ ከአይኤምኤፍ እና ዓለም ባንክ የተገኘው ድጋፍና ብድርም ለሪፎርሙ ትግባራ የሚውል መሆኑን ተናግረዋል፡፡
አበዳሪ ተቋማቱ የሪፎርም ይዘት ጥራት እና የኢትዮጵያን ምርታማነት አቅም በማየት በአፍሪካ ከፍተኛ የተባለ ድጋፍና ብድር መስጠታቸውንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡
እስካሁን ባለው ሂደት ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም እና ዓለም ባንክ 2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ወደ ብሔራዊ ባንክ ገቢ መደረጉንም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ከሁለቱ አበዳሪ ተቋማት ባሻገር ከተለያዩ አጋር አካላት የርዕዮተ ዓለም ልዩነት ሳይገድባት ሪፎርሙን ለማስቀጠል የሚያስችል ሀብት ማግኘቷንም አብራርተዋል።
ከውጭ ከሚገቡ የፍጆታ ዕቃዎች 18 በመቶ ብቻ በውጭ ምንዛሬ እንደሚመጡ ገልፀው፤ ሌሎቹ ግን በአብዛኛው በኢ-መደበኛ ወይም በትይዩ ገበያ ወደ ሀገር ቤት ሲገቡ እንደነበር ገልጸዋል።
በዚህም የምንዛሬ ተመኑ ወደ ገበያ መር መለወጡ በሸቀጦች ዋጋ ላይ ጭማሪ ሊፈጥር እንደማይገባ ገልጸው፤ ሪፎርሙን ተከትሎ ህገ-ወጥነትና አሉታዊ ጫና የሚፈጥሩ ጉዳዮች ከተከሰቱ ህጋዊ ምላሽ ለመስጠት ባንኩ ተገቢውን ዝግጅት ማድረጉንም ጠቁመዋል፡፡
በሌላ በኩል በፋይናንስ ተቋማት ላይ የሚከሰትን ህገወጥ አሰራር ለመቆጣጠር ጥብቅ የፊሲካልና የገንዘብ ፖሊሲ ገቢራዊ እንደሚደረግ ገልጸው፤ በዚህም ቴክኖሎጂን መሰረት ያደረገ ዝግጅት መደረጉን አንስተዋል፡፡