አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 26፣ 2016(ኤፍ ቢ ሲ) የኮሪደር ልማት የነዋሪዎች ትብብርና የመሰረተ ልማት መስሪያ ቤቶች ቅንጅት የተረጋገጠበት ነው ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ፡፡
ከንቲባዋ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባስተላለፉት መልዕክት÷”የአዲስ አበባ ለውጥ ሃብትን በመቆጠብ፣ ለተገቢው የጋራ ልማት ብቻ በማዋል እና ለዜጎች ትኩረት በመስጠት እየተተገበረ ያለ፣ ፈጠራና ፍጥነት ላይ የተመሰረተ እና ቀጣይነት ያለው ነው” ብለዋል።
ስራው የከተማዋ ነዋሪዎች ትብብር ጎልቶ የታየበት እና ከከተማ እስከ ፌደራል ያሉ የመሰረተ ልማት መስሪያ ቤቶች ቅንጅት የተረጋገጠበት መሆኑንም ገልፀዋል፡፡
በኮሪደር ልማት ስራው ህንጻዎችን በከተማዋ ደረጃ እና ዲዛይን መሰረት ያሳመሩ እንዲሁም ለእግረኛ መተላለፊያ እንዲሆን ምቹ በማድረግ የተባባሩ የህንጻ ባለቤቶችን አመስግነዋል፡፡
በተጨማሪም የአገልግሎት ሰጭ ተቋማትን እንዲሁም በአጠቃላይ የኮሪደር ልማቱን ዓላማ ላሳኩ የከተማዋ ነዋሪዎች በከተማ አስተዳደሩ ስም ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ስንተባበር እንዲህ አይነት ፈጣን፣ ሰፊ ፣ ጥራትና ቀጣይነት ያለው ለውጥ ማስመዝገብ እንችላለን ያሉት ከከንቲባዋ ÷ይህ ስራ በሌሎች ከተሞች ተግባራዊ ሲደረግ የተለመደው ቀና ትብብር እንዲደረግ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡