Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ጤናማ ያልሆነ የንግድ እንቅስቃሴ በወንጀል እንደሚያስጠይቅ ተመላከተ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በንግድ ሥርዓቱ ውስጥ ጤናማ ያልሆኑ እንቅስቃሴዎች በአሥተዳደርና በወንጀል የሚያስጠይቁ የሕግ ጥሰቶች መሆናቸው ተገለጸ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ትናንት ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ባደረጉት ውይይት የማክሮ ኢኮኖሚ ለውጡን በቁንጽል ሳይሆን በምልዐት መመልከት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

የሕግ አስፈጻሚ አካላትም የለውጥ ሥራውን ባልተገባ ሕገ-ወጥ መንገድ ለመጠቀም በሚፈልጉ ስግብግብ ነጋዴዎች ላይ ርምጃ እንዲወስዱ ኃላፊነት እንደተሰጣቸው አስረድተዋል፡፡

ይህን በተመለከተ የሕግ ባለሙያው አብነት ዘርፉ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ÷ በንግድ ሥርዓቱ ጤናማ ያልሆኑ እንቅስቃሴዎች በወንጀል የሚያስጠይቁ መሆናቸውንና የግብይት ዕቃዎችን መደበቅ፣ ማከማቸትና መሰወር የደንብ መተላለፍ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

በዚህ ድርጊት ተሳትፈው የሚገኙም ከዓመታዊ ሽያጫቸው ከ5 እስከ 10 በመቶ ቅጣት እንዲሁም እስከ አምስት ዓመት የሚደርስ ፅኑ እስራት እንደሚጠብቃቸው ነው ያስረዱት፡፡

የኑሮ ውድነት እንዲፈጠር እንዲሁም ሰው ሠራሽ የዋጋ ንረት መፍጠር በተመሳሳይ የሕግ ተጠያቂነት ያስከትላል ብለዋል፡፡

በንግድ ሥራ ላይ ያልተሰማሩ ቢሆኑም የድርጊቱ ተባባሪ ሆነው ከተገኙ እስከ 50 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣትና እስከ 5 ዓመት የሚደርስ ጽኑ እስራት ቅጣት ያስከትላል ነው ያሉት፡፡

በመሆኑም የንግዱ ማኅበረሰብና ሸማቹ የንግድ እንቅስቃሴውን ሕጋዊ አካሄድ በመረዳት መብትና ግዴታቸውን ማወቅ እንደሚገባቸው መክረዋል፡፡

በሀሪቷ የተረጋጋ ገበያና ቀጣይነት ያለው የምጣኔ ሃብት ዕድገት እንዲኖር መንግሥት ሕግ የማስከበር ሥራውን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አመላክተዋል፡፡

Exit mobile version