ጤና

የወባ በሽታን ለመቆጣጠር ጠንካራ የክትትልና ቁጥጥር ስራ እየተሰራ ነው – ጤና ሚኒስቴር

By Meseret Awoke

July 31, 2024

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የወባ በሽታን ለመቆጣጠር ጠንካራ የክትትል እና ቁጥጥር ስራ እየተሰራ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ የወባ፣ የኮሌራና የኩፍኝ ስርጭትን በሚመለከት መግለጫ ሲሰጡ እንዳሉት፥ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት የበሽታው ስርጭት እየቀነሰ መጥቷል፡፡

ሆኖም ግን ወባ ጠፍቷል በሚል በማህበረሰቡ የግንዛቤ ክፍተት እና በሌሎች ምክንያቶች የበሽታው ስርጭት ባለፈው አንድ ዓመት እየጨመረ በመምጣቱን ጠቁመዋል።

ይህንን ተከትሎም አሁን ላይ የወባ በሽታ ስርጭት በጨመረባቸው 220 ወረዳዎች ላይ የክትትል፣ የምልከታና የቁጥጥር ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል ሚኒስትሯ።

ከክልሎች ጋር በየሣምንቱ የበሽታውን ስርጭት በመከታተል የበሽታ ቁጥጥር ስራ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች በቂ ግብዓቶችን ወደ ጤና ተቋማት የማዳረስ ስራ እየተከወነ መሆኑን ተናግረው፥ በዚህም የመድሃኒትና የግብዓቶች ስርጭት እንዲጨምር ተደርጓል ነው ያሉት።

በባለፈው አንድ ወር ከ700 ሺህ በላይ ዜጎች ህክምና ማግኘታቸውን ያነሱት ሚኒስትሯ፥ ወደ 2 ነጥብ 7 ሚሊየን ዜጎችን ማከም የሚያስችሉ መድሃኒቶች ወደ ሀገር ውስጥ መግባታቸውን ጠቅሰዋል።

ባለፉት ሶስት ዓመታትም ከ30 ሚሊየን በላይ አጎበር መሰራጨቱን ገልጸው፥ ባለፈው ሣምንት ደግሞ ከ500 ሺህ በላይ አጎበር በመግባቱ ይሰራጫል ተብሏል ።

ከ7 ሚሊየን በላይ ፈጣን የመመርመሪያ ኪቶች እንዲገቡ መደረጋቸው ጠቅሰው፥ ባለፉት ቀናት ከ1 ነጥብ 8 ሚሊየን በላይ ቤቶች የኬሚካል ርጭት መካሄዱንም ነው የጠቆሙት።

እንደ ሀገር አሁን ያለው የወባ በሽታ ስርጭት ወረርሽኝ የሚባልበት ደረጃ ላይ እንዳልደረሰም ገልጸዋል፡፡

2016 ዓ.ም በ152 ወረዳዎች ላይ የኮሌራ በሽታ ተከስቶ እንደነበር አስታውሰው፥ አሁን ላይ በአምስት ክልሎችና በ109 ወረዳዎች መቆጣጠር መቻሉንም ነው የጠቆሙት።

በቀሪ 43 ወረዳዎች ላይ ደግሞ ክትትል እየተደረገ መሆኑን የጠቆሙት ሚኒስትሯ፥ 904 ጊዜያዊ የህክምና ማዕከላት ተቋቁሞ ሲሰራ እንደነበር ጠቅሰዋል።

በመሳፍንት እያዩ