አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር እና ተጠሪ ተቋማቱ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ በመሬት መንሸራተት አደጋ ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች ድጋፍ አደረጉ።
የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም (ዶ/ር)÷ በተቋማቱ የተደረገውን የ10 ነጥብ 7 ሚሊየን ብር ድጋፍ በተረከቡበት ወቅት፤ የአደጋ ተጎጂዎችን ለመደገፍና በዘላቂነት ለማቋቋም የተቀናጁ ተግባራት እየተከናወኑ ነው ብለዋል።
ለመልሶ ማቋቋምና አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ እየተደረገ ያለው ርብርብም ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል።
በዛሬው ዕለትም በመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር እና ተጠሪ ተቋማቱ ለተደረገው ድጋፍ አመስግነዋል።
በክረምቱ መደበኛና ከመደበኛ በላይ ዝናብ በሚኖርባቸው አካባቢዎች አደጋ እንዳይከሰት ጥንቃቄ እንዲደረግም አስገንዝበዋል፡፡
ሊደርስ ከሚችል አደጋ አስቀድሞ ለመከላከል ጥረት እየተደረገ መሆኑን ስለመግለፃቸውም ኢዜአ ዘግቧል።
የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ሀብታሙ ኃይለሚካኤል÷ በአደጋው ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች መልሶ ለማቋቋም የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።
በተመሳሳይም የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት በጎፋ ዞን በመሬት መንሸራተት አደጋ ለተጎዱ ወገኖች ከ3 ሚሊየን ብር በላይ የሚሆን ድጋፍ ማድረጉን ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡