የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያና ኡጋንዳ በቀጣናዊ የደኅንነትና ጸጥታ ጉዳዮች ዙሪያ የትብብር ሥራዎችን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገለፁ

By Meseret Awoke

July 30, 2024

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያና ኡጋንዳ በቀጣናዊ የደኅንነትና ጸጥታ ጉዳዮች ዙሪያ በጋራ እያከናወኗቸው ያሉ የትብብር ሥራዎችን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል፡፡

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት እና የኡጋንዳ የውጭ ደኅንነት ተቋማት በቀጣናዊ የደኅንነትና ጸጥታ ጉዳዮች ዙሪያ በጋራ እያከናወኗቸው ያሉ የትብብር ሥራዎችን በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባ ገምግመዋል፡፡

የኢትዮጵያና ኡጋንዳ የመረጃና ደኅንነት ተቋማት ቀደም ሲል በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና የደኅንነትና የጸጥታ ስጋት የሆኑትን ሽብርተኝነት፣ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን፣ ሕገወጥ ታጣቂዎችንና ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል የሁለትዮሽ ስምምነት መድረሳቸው ይታወሳል፡፡

ይህን ስምምነት በመተግበር የተገኙ ውጤቶችና ቀጣይ መጠናከር ባሉባቸው ጉዳዮች ዙሪያ በዝርዝር ነጥቦች ላይ ተወያይተዋል ነው የተባለው።

በአገልግሎቱ በኩል የውጭ መረጃ ዘርፍ ም/ዳይሬክተር ጀነራል ታዜር ገ/እግዚአብሔር እንዲሁም በኡጋንዳ በኩል ደግሞ የውጭ ደኅንነት ተቋም ዳይሬክተር ጀነራል ጆሴፍ ኦኬሎ የጋራ ውይይቱን መርተዋል፡፡

ም/ዳይሬክተር ጀነራል ታዜር እንደገለጹት ፥ የሀገሪቱ የውጭ አቻ የመረጃ ተቋም ከመረጃ ልውውጥና ከደኅንነት አኳያ ከአገልግሎት መሥሪያ ቤቱ ጋር የጀመረውን አጋርነት አጠናክሮ ለመቀጠል እያሳየ ያለው ቁርጠኝነት የሚደነቅ ነው ብለዋል፡፡

የኡጋንዳ የውጭ ደኅንነት ተቋም ዳይሬክተር ጀነራል ጆሴፍ ኦኬሎ በበኩላቸው ፥ ኢትዮጵያ በጎረቤት ሀገራት እና በቀጣናው ዘለቂ ሰላም እንዲረጋገጥ እየሠራች መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

በዚህም የሁለቱ ሀገራት የመረጃ ተቋማት ሕገወጦችን ተከታትለውና ለይተው ተጠያቂ በማድረግ ለዘላቂ ሰላም ምቹ መደላድል ለመፍጠር የጀመሩትን ትብብር አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ነው ያረጋገጡት፡፡

ሁለቱ አቻ የመረጃ ተቋማት የዛሬ ሁለት ዓመት በጋራ ለመሥራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት መፈራረማቸው ይታወሳል፡፡