Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በሕንድ በደረሰው የመሬት መንሸራተት አደጋ ህይወታቸውን ያጡ ሰዎች ቁጥር 93 ደረሰ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሕንድ ደቡባዊ ግዛት ኬራላ የጣለው ከባድ ዝናብ ባስከተለው የመሬት መንሸራተት አደጋ ህይወታቸውን ያጡ ሰዎች ቁጥር 93 ሲደርስ ፤ ብዙዎች ከመሬት ስር ተቀብረው ሊሆን እንደሚችል ተሰግቷል፡፡

እየተከናወነ ያለውን የነፍስ አድን ሥራም ከባድ ዝናብና የድልድይ መደርመስ እያስተጓጎለው መሆኑን ተከትሎ አደጋው በተከሰተበት ሥፍራ ያሉ ዜጎችን ለማውጣት አዳጋች እንዳደረገው ተሰምቷል፡፡

በዚህም አደጋ የሟቾች ቁጥር ያሻቅባል የሚል ስጋት እንዳለ የተገለጸ ሲሆን፥ ይህም በአካባቢው በፈረንጆቹ 2018 ከደረሰው ከባድ የጎርፍ አደጋ በኋላ አስከፊው ነው ተብሏል፡፡

የነፍስ አድን ሥራ ለመስራትም ከ200 በላይ የሠራዊት አባላት መሰማራታቸውም ነው የተጠቆመው፡፡

የሀገሪቱ አንድ ባለስልጣን በሰጡት መግለጫም፥ የደረሰው የመሬት መንሸራተት አደጋ መላውን አካባቢ ጠራርጎ ወስዶታል ብለዋል፡፡

በአካባቢው ባሉ ሆስፒታሎችም ቢያንስ 123 ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች የህክምና ክትትል እየተደረገላቸው እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፥ ከ3 ሺህ በላይ ሰዎች ደግሞ ከአካባቢው እንዲለቁ በማድረግ ወደ 45 የእርዳታ ካምፖች መግባቸውን የዘገበው ቢቢሲ ነው፡፡

ከክስተቱ በኋላ በተደረገ አሰሳም የ16 ሰዎች አስከሬን በወንዝ ውስጥ መገኘቱ የአደጋውን አስከፊነት የሚያሳይ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ግዛቲቱ በተለይ በክረምት ወራት ለመሬት መንሸራተት አደጋ የተጋለጠች መሆኗም ይገለጻል፡፡

Exit mobile version