Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በአውሮፓ 30 በመቶ የኃይል አቅርቦት በነፋስና በፀሐይ ኃይል መተካቱ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በፈረንጆቹ 2024 የመጀመሪያ አጋማሽ 13 የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት ከድንጋይ ከሰል እና ከጋዝ ይልቅ ከነፋስ እና ከፀሀይ የበለጠ የኤሌክትሪክ ኃይል ማግኘታቸውን ሪፖርት አመላክቷል።
 
በ2024 የመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት ውስጥ ከከሰል፣ ነዳጅ እና ጋዝ የሚመነጨው ኃይል በ17 በመቶ መቀነሱን ዓለም አቀፉ የአየር ንብረት ትንበያ ኢምበር አስታውቋል።
 
ከ 2022 የመጀመሪያ አጋማሽ ጀምሮ ከበካይ ጋዞች ለመውጣት የሚደረገውን ጥረት በማስቀጠል በዘርፉ የበካይ ጋዝ ልቀት መጠንን በአንድ ሦስተኛ ለመቀነስ እንደተቻለም ጠቁሟል፡፡
 
የኢምበር የአየር ትንበያ ተንታኝ ክሪስ ሮስሎው የንፋስ እና የፀሐይ መጨመር ታዳሽ ያልሆኑ የኃይል አማራጮችን ሚና እያጠበበው መምጣቱን ገልጸዋል።
 
ሪፖርቱ እንዳመላከተው÷ የአውሮፓ ህብረት ከ 2023 የመጀመሪያ አጋማሽ እስከ 2024 የመጀመሪያ አጋማሽ ድረስ ከ24 በመቶ ያነሰ የድንጋይ ከሰል እና ከ14 በመቶ ያነሰ ጋዝ ለኃይል ጥቅም ላይ አውለዋል፡፡
 
ለውጡ የመጣው የኤሌክትሪክ ፍላጎት አነስተኛ ቢሆንም ለሁለት ዓመታት በዘለቀው በኮቪድ 19 ወረርሽኝ እና የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ጋር ተያይዞ በተከሰተ የአቅርቦት ማሽቆልቆል የተነሳ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
 
ተንታኙ አያይዘውም አባል ሀገራቱ በነፋስ እና በፀሐይ ኃይል የማመንጨት ሂደትን ከቀጠሉ ታዳሽ ባልሆኑ የኃይል ምንጮች ላይ ካላቸው ጥገኝነት እንደሚላቀቁ ማረጋገጣቸውን ዘጋራዲያን ዘግቧል፡፡
Exit mobile version