አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በኦሊምፒክ ውድድር የተሳተፈችው በአውስትራሊያ ሜልቦርን በፈረንጆቹ 1956 በተካሄደው 16ኛው ኦሊምፒክ ነው፡፡
ምንም እንኳን ኦሊምፒክ በፈረንጆቹ 1896 ቢጀመርም ኢትዮጵያ በውድድሩ ላይ የተሳተፈችው ከ60 ዓመታት በኋላ መሆኑን መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡
የኦሊምፒክ ጨዋታ ከተጀመረ ጊዜ ጀምሮም በ14 ውድድሮች ላይ መሳተፍ ችላለች፡፡
በተሳትፎዋም 23 የወርቅ፣ 12 የብር እና 23 የነሐስ በአጠቃላይ 58 ሜዳሊያዎችን በአትሌቲክስ ዘርፍ በ36 ብርቱ አትሌቶቿ አማካኝነት ሰብስባለች፡፡
በፈረንሳይ ፓሪስ አስተናጋጅነት እየተካሄደ በሚገኘው 33ኛው ኦሊምፒክም ኢትዮጵያ በተለያዩ የስፖርት ዘርፎች ትሳተፋለች፡፡
በውድድሩም ኢትዮጵያን ጨምሮ 206 ሀገራት እንደሚሳተፉ እና 10 ሺህ 500 ስፖርተኞች በ32 የስፖርት ዓይነቶች እንደሚወዳደሩ ይጠበቃል፡፡
ኢትዮጵያም በ15ኛ የኦሊምፒክ ውድድሯ በአትሌቲክስና ውኃ ዋና ስፖርቶች 38 ስፖርተኞችን ታሳትፋለች።
ቀነኒሳ በቀለ፣ ሰለሞን ባረጋ፣ በሪሁ አረጋዊ እና ለሜቻ ግርማ፤ ጉዳፍ ፀጋይ፣ ትዕግስት አሰፋና ፅጌ ዱጉማ በሴቶች በ33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ኢትዮጵያን ወክለው ከሚሳተፉ አትሌቶች መካከል ይጠቀሳሉ።
በኦሊምፒክ ጨዋታዎች ላይ የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን ሐምሌ 15 ቀን 2016 ዓ.ም በብሔራዊ ቤተ መንግስት ሽኝት መደረጉ ይታወሳል፡፡
በዚሁ ወቅትም ፕሬዚዳንት ሳኅለወርቅ ዘውዴ ባስተላለፉት መልዕክት አትሌቶች በ33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ከምንም በላይ ኢትዮጵያን በማስቀደም ሀገራቸውን ስኬታማ ለማድረግ መትጋት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
ኢትዮጵያን ወክለው በኦሊምፒክ ጨዋታዎች ላይ የሚሳተፉ ስፖርተኞች ከሚያዝያ ወር 2016 ዓ.ም አንስቶ ለውድድሩ ዝግጅት ሲያደርጉ መቆየታቸውን የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ መረጃ አመላክቷል፡፡
መልካም ዕድል ለኢትዮጵያ!!