አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) እስራኤል በደቡባዊ ሊባኖስ በሚገኙ ዘጠኝ ከተሞች ላይ ከበድ ያለ ጥቃት መፈፀሟ ተገለፀ፡፡
እስራኤል በደቡባዊ ሊባኖስ በሚገኙት ሁዎላ፣ ማርካቢ፣ አይታ አል ሻብ፣ ኪሃም፣ ሻኸን፣ ያሩን፣ ማይስ አል ጀበል፣ ኬፈርኬላ እና ቦር አል ሻማሊ በተባሉ ከተሞች ነው መጠነ ሰፊ ጥቃት መሰንዘሯ የተገለፀው።
ጥቃቱ ሂዝቦላህን ለማዳከም ያለመ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን የእስራኤልን መጠነ ሰፊ ጥቃት ተከትሎ በአካባቢው ያለው ውጥረት የበለጠ መባባሱ ተገልጿል፡፡
ጥቃቱ ባለፈው ቅዳሜ በእስራኤል ጎላን ተራሮች ላይ ከሂዝቦላህ ተተኩሷል በተባለ የሚሳኤል ጥቃት 12 ሰዎች መሞታቸውን ተከትሎ የተወሰደ የአፀፋ ምላሽ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
እስራኤል በጎላን ተራሮች በምትገኘው የማይዳል ሻምስ ከተማ ላይ የተፈፀመው የሚሳኤል ጥቃት ከሂዝቦላህ የተተኮሰ መሆኑን አስታውቃለች።
ሂዝቦላህ በበኩሉ ጥቃቱን እንዳልፈፀመ ገልፆ፤ በጉዳዩ ላይ ገለልተኛ ምርመራ እንዲደረግ ጠይቋል፡፡
ጥቃቱን ተከትሎ የሊባኖስ መንግስት ባወጣው መግለጫ÷ ንፁሃንን የቀጠፈውን የማይዳል ሻምስ ከተማ ጥቃት በማውገዝ በሂዝቦላህ እና በእስራኤል መካከል የተኩስ አቁም እንዲደረግ ጥሪ አቅርቧል።
ሬውተርስን ጠቅሶ አረብ ኒውስ እንደዘገበው÷ ሂዝቦላህ ከምስራቅ እና ደቡባዊ ሊባኖስ ከሚገኙ ቁልፍ ወታደራዊ ቦታዎች ለቆ ቢወጣም ቡድኑ በእስራኤል ላይ ጥቃት ለመፈፀም አሁንም በተጠንቀቅ ላይ ይገኛል፡፡
በቡደኑ እና በእስራኤል መካከል በተፈጠረው ግጭት ምክንያት በቀጠናው ከባድ ውጥረት መፈጠሩ የተገለፀ ሲሆን፤ ፈረንሳይ እና ኖርዌይ ዜጎቻቸው ወደ እስራኤልና ሊባኖስ እንዳይጓዙ ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል፡፡