Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የቀን ክፉ ሙሉ ቤተሰቦቼን አሳጥቶኝ እርቃኔን ቀረሁ – ሠላምነሽ አስራት

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 21፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ የመሬት መንሸራተት አደጋ በደረሰበት ቅጽበት ቤተሰቦቿን በሙሉ ያጣችው ሠላምነሽ አስራት የኢትዮጵያውያንን እገዛ ትፈልጋለች።

ሠላምነሽ ኑሮዋ በሳውላ ከተማ ሲሆን ቤተሰቦቿ አሁን ኢትዮጵያ ሀዘን እንድትቀመጥ ባደረገው ኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ ይኖራሉ።

የዚህ አካባቢ አደጋ በተከሰተበት ወቅት በተኛችበት ስልኳ ያቃጭላል።

የስልኳን ጥሪ ሰምታ ከእንቅልፏ ከተነሳች በኋላ ስልኳን ስታነሳ በተወለደችበት ቀዬ አደጋ ደርሷል የሚል ድምጽ ነበር የሰማችው።

በድንጋጤ የፈዘዘቺው ሰላምነሽ÷ ወደ ትውልድ ቀዬዋ ብታመራ እናት፣ አባት፣ እህት፣ ወንድም ከነቤታቸው ከነማሣቸው በተከሰተው የመሬት መንሸራተት አደጋ መዋጣቸውን ተረዳች።

አሁን ብቻዬን ቀርቻለሁም ስትልም ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግራለች።

ሰባት ቀን ሙሉ በተደረገ ፍለጋ እናትና እህቷ ከናዳው ክምር ተገኝተው ወጥተው ትንሽም ቢሆን እርሟን አውጥታለች።

እስከ አሁን ግን አባትና ታናሽ ወንድሟ ከተቀበሩበት የአፈር ክምር አስክሬናቸውን ማግኘት አለመቻሉ ጨርሳ እርሟን እንዳታወጣ አድርጓታል።

ሀዘኗን የከፋ ያደረገው ደግሞ ቤተሰቦቿን ለማዳን ብሎ የተሰበሰበው ሕዝብ ማለቁ መሆኑን ታነሳለች።

በታሪኩ ለገሰ፣ መለሰ ታደለ እና ማቱሳላ ማቲዎስ

Exit mobile version