የሀገር ውስጥ ዜና

መከላከያ ሚኒስቴር በመሬት መንሸራተት ለተጎዱ ወገኖች ድጋፍ አደረገ

By Tamrat Bishaw

July 28, 2024

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 21፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) መከላከያ ሚኒስቴር በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ በደረሰው የመሬት መንሸራተት ለተጎዱ ወገኖች ከ6 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት የዕለት ደራሽ ምግብና ቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል።

ድጋፉን በስፍራው በመገኘት ያስረከቡት የመከላከያ ሚኒስቴር ህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ኮሎኔል ጌትነት አዳነ÷ በአደጋው መስዋዕትነት የከፈሉት ወገኖቻቸውን ለማትረፍ ሲሉ በመሆኑ ከመከላከያ ሰራዊቱ ተልዕኮ ጋር ያመሳስለዋል ብለዋል።

በአደጋው ለተጎዱ ወገኖች የ6 ሚሊየን 305 ሺህ ብር ድጋፍ አምጥተናል ብለዋል።

የሀገር መከላከያ ሰራዊት የደቡብ እዝ ፈጥኖ በመድረስ ከራሳቸው ሬሽን በመቀነስ ድጋፍ ማድረጉን ያስታወሱት ደግሞ የዞኑ አስተዳዳሪ ዳግማዊ አየለ (ኢ/ር) ሲሆኑ አሁንም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሌላ ድጋፍ በማድረጉ ምስጋና አቅርበዋል።

በታሪኩ ለገሰ፣ መለሰ ታደለ እና ማቱሳላ ማቲዎስ