የሀገር ውስጥ ዜና

የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ዘርፉ ለሀገር ምጣኔ ሀብታዊ እንቅስቃሴ ትልቁን ድርሻ እየተወጣ ነው- ዓለሙ ስሜ(ዶ/ር)

By Tamrat Bishaw

July 28, 2024

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 21፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ዘርፉ ለሀገር ምጣኔ ሀብታዊ እንቅስቃሴ ትልቁን ድርሻ እየተወጣ ነው ሲሉ የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክ ሚኒስትሩ ዓለሙ ስሜ(ዶ/ር) ተናገሩ፡፡

“የዜጎችን ክብርና ደሕንነት ያረጋገጠ ጉዞ” በሚል መሪ ሀሳብ በትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ዘርፍ የሚሰጡ አገልግሎቶችን በማሻሻል ላይ ያተኮረ የንቅናቄ መድረክ በአዳማ እየተካሄደ ነው።

በመድረኩ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ(ዶ/ር)÷ ዘርፉ በወጪ ገቢ ምርቶች የሀገሪቱ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት ነው ብለዋል።

የየብስን ጨምሮ የአየር እና የባቡር ትራንስፖርትን የሚያካትን መሆኑን የጠቆሙት ሚኒስትሩ÷ የዘርፉ ተዋንያን በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ሆነው ሀገራዊ ኃላፊነታቸውን እየተወጡ ይገኛሉ ብለዋል።

ይሁንና በአገልግሎቱ የሚስተዋሉ ብልሹ አሰራርና የመልካም አስተዳደር ዕጦቶች የዘርፉ ፈተናዎች ናቸው ብለዋል።

ያለብቃት መንጃ ፈቃድ የሚሰጡ ተቋማትና ለዚህ ተባባሪ የሆኑ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች እንዲሁም የተሽከርካሪዎቻቸውን ደህንነት ሳያረጋግጡ አገልግሎት የሚሰጡ መኖር የዘርፉን መልካም ገፅታ አጠልሽቷል ነው ያሉት ።

የንቅናቄ መድረኩም በዚሁ ዘርፍ ግንዛቤ ለመፍጠር ያለመ መሆኑን አንስተዋል።

በመድረኩ ሚኒስትር ዴኤታዎች ፣የክልል ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊዎች ፣ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች እና ከተለያዩ ክልሎች የተወጣጡ ሴቶች እየተሳተፉ ነው፡፡

በወንድሙ አዱኛ ፣መሳፍንት እያዩ እና ህይወት አበበ