አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከሰሞኑ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ የተከሰተው የመሬት መንሸራተት አደጋ የበርካታ ወገኖችን ሕይወት ቀጥፏል፤ ወላጅን ከልጅ ለይቷል፡፡ ብዙዎችንም አፈናቅሏል፡፡
ገና ስም እንኳን ያልወጣለት፣ ጡት ጠግቦ ያልጠባ የሦስት ወር ዕድሜ ያለው ሕጻንም ይኸው አደጋ አባት እና እናቱን ነጥቆ ብቸኛ አድርጎታል፡፡
በዕለቱ የ60 ሺህ ብር እቁብ የደረሳት እናት ታመነች ዳንኤል ብሩን ይዛ ወደቤት ስትገባ፤ አባት እዝቅኤል ሰለሞን ሕጻኑን እቤት እየጠበቀ በነበረበት ሁኔታ በአካባቢው የመሬት መንሸራተት አደጋ ሲከሰት የሰሙትን ከፍተኛ ጩኸት ተከትለው ወገኖቻቸውን ለመታደግ ወደ ቦታው ያቀናሉ፡፡
የሕጻኑ አጎት መስፍን ኦይላ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳሉት÷ አደጋው ወደ ተከሰተበት ቦታ የሄዱትም አባት የሦስት ወር ልጁን እቤት ውስጥ ትቶ፤ እናትም የተቀበለችውን የእቁብ ብር እንደያዘች ነበር፡፡
በወቅቱ በአደጋው ጉዳት የደረሰበትን የእናት አጎት ለማትረፍ መረባረብ የጀመሩት የሕጻኑ ወላጆችም በዚያው ቀርተዋል ብለዋል፡፡
የሦስት ወር ዕድሜ ያለው ሕጻንም እንመለሳለን ብለው በልጃቸው ላይ በሩን እንደዘጉ በዚያው አሸለቡ፤ ሕጻኑ እናትና አባቱን በለቅሶ ቢጣራም ሊደርሱለት አልቻሉም ነው የሚሉት፡፡
አሁን ላይም በአያቶቹ እጅ ላይ እንደሚገኝ ነው አቶ መስፍን የገለጹት፡፡
በታሪኩ ለገሰ