አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በፓሪስ የኦሊምፒክ መክፈቻ ሥነ-ስርዓት ላይ የደቡብ ኮሪያ አትሌቶች በስህተት ሰሜን ኮሪያ ተብለው ከተዋወቁ በኋላ የኦሊምፒክ አዘጋጆቹ ይቅርታ መጠየቃቸው ተሰምቷል።
ሀገራቸውን ወክለው ለኦሊምፒክ ሊሳተፉ በፓሪስ የከተሙት ደቡብ ኮሪያውያን በሴን ወንዝ ላይ ሰንደቅ ዓላማቸውን እያውለበለቡ ሲያልፉ ነበር፡፡
በዚህም ጊዜ የፈረንሳይኛ እና የእንግሊዘኛ ቋንቋ የመድረክ አጋፋሪዎች በስህተት “የሰሜን ኮሪያ ህዝባዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ” ሲሉ የሰሜን ኮሪያን ስም ጠርተው አስተዋውቀዋል ነው የተባለው፡፡
ሆኖም የሰሜን ኮሪያ ልዑካንን ግን በትክክል መጠሪያቸው እንደጠሯቸው ተገልጿል፡፡
እንደሚታወቀው ሁለቱ ኮሪያዎች ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ በኋላ ለሁለት የተከፈሉ ሲሆን፥ በሀገራቱ ያለው የእርስ በርስ ውዝግብ መቀጠሉን የዘገበው ቢቢሲ ነው፡፡
የደቡብ ኮሪያ ስፖርት ሚኒስቴር፥ በመንግስት ደረጃ ለፈረንሳይ ቅሬታ ለማቅረብ ማቀዱን ገልጿል።
የ2008 የኦሊምፒክ ክብደት ማንሳት ሻምፒዮን የሆነው የሁለተኛው ምክትል ስፖርት ሚኒስትር ጃንግ ሚ-ራን ከኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ቶማስ ባች ጋር እንዲገናኙ መጠየቁን መግለጫው አክሏል።
የዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ በኤክስ ገጹ ላይ፥ ለተፈጠረው ስህተት ይቅርታ ጠይቋል።
በመደበኛነት የኮሪያ ሪፐብሊክ በመባል የምትታወቀው ደቡብ ኮሪያ ዘንድሮ 143 አትሌቶችን በኦሎምፒክ ቡድኗ ያቀፈች ሲሆን፥ በ21 ስፖርቶች እንደሚወዳደሩም ነው የተጠቆመው።
ሰሜን ኮሪያ 16 አትሌቶችን ስትልክ፥ ከሪዮ 2016 ኦሊምፒክ በኋላ በጨዋታዎች ስትሳተፍ ይህ የመጀመሪያው ነው ተብሏል።