አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ ለደረሰው የመሬት መንሸራተት አደጋ ለተጎዱ ዜጎች የሚሆን የሰብዓዊ ድጋፍ አድርጓል፡፡
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ ዛሬ በሰጡት መግለጫ፥ የተባበሩት መንግስታትና የተለያዩ ሀገራት መሪዎች በሀገሪቱ ለደረሰው የመሬት መንሸራትት አደጋ የተሰማቸውን ሃዘን መግለጻቸውን ጠቁመዋል፡፡
ዛሬ ማለዳ ደግሞ የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች በጎፋ ለደረሰው አደጋ የሰብዓዊ ድጋፍ መላኩ የተገለጸ ሲሆን ፥ ድጋፉ 75 ቶን ምግብ ነክና ሌሎች ቁሳቁሶችን ያካተተ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
ይህም የሰብዓዊ ድጋፍ ጭነት ዛሬ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ መድረሱም ነው የተነገረው፡፡
የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች ዛሬ ብቻ ሳይሆን በደስታም ጊዜ ከኢትዮጵያ ጋር እያደረገች ላለው አጋርነት አገልግሎቱ ምስጋናውን አቅርቧል፡፡
ይህን ድጋፍ የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ተረክቦ ለተጎጂዎች እንደሚያደርስም ተጠቁሟል፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘ እስካሁን ባለው መረጃ በአደጋው ለህልፈት የተዳረጉ ዜጎች አስከሬን 231 መድረሱ የተገለጸ ሲሆን፥ 18 ሰዎች አስከሬን አለመገኘቱም ተጠቅሷል፡፡
አሁንም ተጎጂዎችን የመፈለጉ ስራ እንደቀጠለ ሲሆን፥ በአደጋው ከ500 በላይ የሆኑ ሰዎች ከመኖሪያ ቦታቸው ተፈናቅለዋል ተብሏል በመግለጫው፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞ ከ6 ሺህ በላይ የሚሆኑ ዜጎች ተመሳሳይ አደጋ እንዳይደርስባቸው ግብረ-ሃይል ተቋቁሞ ጥናቶች እየተደረጉ እንደሚገኙ ተነስቷል፡፡
እስካሁንም ለከተጎጂ ወገኖች የተለያዩ አካላት ድጋፍ ማድረጋቸውንም ነው በመግለጫው የተነሳው፡፡
በዚህም አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች በሙሉ መንግስት የተሰማውን ሃዘን ዳግም የገለጸ ሲሆን፥ በአደጋው የተጎዱ ዜጎችን በማጽናናትና ድጋፍ በማድረግ ለተሳተፉ ሁሉ ምስጋናውን አቅርቧል፡፡