አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በትግራይ ክልል በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ከ53 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በችግኝ እንደሚሸፈን የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ቢሮ ገለጸ።
በቢሮው የደን ልማት፣ ጥበቃና አጠቃቀም ዳይሬክተር አቶ ተስፋይ ተክለሃይማኖት እንደገለጹት፤ በዘንድሮ ክረምት የሚተከለውን ችግኝ ለመንከባከብ እና ለመጠበቅ የተከላ ካርታ ተዘጋጅቶ እየተሰራ ነው፡፡
ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው የፍራፍሬ ችግኞችን ጨምሮ የደን፣ የከተማ ውበት ለመጨመር እና ስነ ምህዳርን ለመጠበቅ የሚያስችሉ ችግኞች እየተተከሉ መሆናቸውን አብራርተዋል።
በክልሉ በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ከ53 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ለመሸፈን 33 ሚሊየን ችግኞች መዘጋጀታቸውንና ወደ ተግባር መገባቱን ገልፀዋል።
እስከ አሁን 19 ሚሊየን 668 ሺህ ችግኞች በተዘጋጀላቸው ቦታ እንደተተከሉም ተናግረዋል፡፡
የከተማና የገጠር ነዋሪው ማህበረሰብ፣ የመንግስትና የግል ሰራተኞች፣ የስፖርት ማህበረሰብ እንዲሁም የጸጥታ አካላት በችግኝ ተከላ መርሐ ግብሩ ላይ ተሳትፎ እያደረጉ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡
በዚህም የተያዘውን እቅድ ለማሳካት ሰፊ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን መግለጻቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።
ነሐሴ 13 ቀን 2016 በአንድ ጀምበር 900 ሺህ ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡