አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) መንግስት የጎንደር ከተማን ህዝብ የረጅም ጊዜ ጥያቄ የሚመልሱ የልማት ስራዎች ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን የከተማዋ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ባዩህ አቡሃይ ተናገሩ።
መንግስት በጎንደር ከተማ እያከናወናቸው ያሉ የልማት ስራዎችን በመደገፍ ለመንግስት እውቅና በመስጠት ምስጋና ለማቅረብ ህዝባዊ ሰልፍ ተካሂዷል።
የድጋፍ ሰልፉ በተለይ የፌደራል መንግስት ለከተማዋ ልማት ትኩረት በመስጠት ተቋርጠው የነበሩ ፕሮጀክቶች በማስቀጠል፣ አዳዲስ ፕሮጀክቶችን በመጀመሩ ለመንግስት እውቅና መስጠትና መደገፍን ዓላማው አድርጓል።
የከተማዋ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ባዩህ አቡሃይ ህዝባዊ የድጋፍ ሰልፉን መጠናቀቅ አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ፥ መንግስት የከተማዋን ሁለንተናዊ እድገት የሚያረጋግጡ የልማት ፕሮጀክቶች እየተካሄዱ እንደሆነ አንስተዋል።
እድሜ ጠገብ፣ ታሪካዊና ጥንታዊ በሆነችው የጎንደር ከተማ በህዝቡ በርካታ የልማት ጥያቄዎች ለዘመናት ሲቀርቡ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።
ከእነዚህም መካከል የንፁህ ውሃ መጠጥ አቅርቦት ችግሮች እና ሌሎችም የልማት ጥያቄዎች እንደነበሩ አውስተዋል።
እነዚህን መሠረታዊ ጥያቄዎች ለመፍታት በተለይ ከለውጡ ወዲህ መንግስት በሰጠው ሰፊ ትኩረት የመገጭ የውሃ ፕሮጀክትና በከተማዋ የንግድ እንቅስቃሴን የሚያሳልጡ የመንገድ ፕሮጀክቶች እየተሰሩ መሆኑን አብራርተዋል።
እነዚህንና መሰል ፕሮጀክቶችን ለማስቀጠል ሰላምን ማስጠበቅ እንደሚገባም ጠቅሰው ፥ በጫካ የገቡ ወንድሞችም መንግስት ያቀረበውን የሰላም ጥሪ ተቀብለው ወደልማት እንዲገቡ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።
በሳሙኤል ወርቃየሁ