አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በይርጋለም የተቀናጀ የግብርና ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ እያለሙ ከሚገኙ እና ከአዳዲስ ባለሃብቶች ጋር የኢንቨስትመንት ምክክር መድረክ በአዲስ አበባ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።
መድረኩን የሲዳማ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ኮርፖሬሽን ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴርና ከተባበሩት መንግስታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት (ዩኒዶ) ጋር በመተባበር እንዳዘጋጀው ተገልጿል።
በመድረኩ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳር ደስታ ሌዳሞ፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል፣ የልማት ባንክ የስራ ኃላፊዎች፣ የፌደራልና የክልል የስራ ኃላፊዎች እንዲሁም አጋር አካላትና ባለሀብቶች ተገኝተዋል።
አቶ ደስታ ሌዳሞ በወቅቱ እንደተናገሩት፥ መሠረተ ልማቶች ተሟልተውለት አልሚ ባለሀብቶችን እየተጠባበቀ በሚገኘው በይርጋለም የተቀናጀ የግብርና ኢንዱስትሪ ፓርክ አዳዲስ ባለሃብቶች ቢገቡ ውጤታማ ይሆናሉ።
ክልሉም ለፓርኩ አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ በኩል ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠዋል።
አቶ መላኩ አለበል በበኩላቸው፥ የይርጋለም የተቀናጀ የግብርና ኢንዱስትሪ ፓርክን ጨምሮ 32 ቢሊየን ብር ወጪ በማድረግ ፓርኮች እንደተገነቡ ገልፀዋል።
ፓርክ ከመገንባት ባሻገር ለአምራቾች ምቹ ሁኔታ ለመፍጠርም ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።
የይርጋለም የተቀናጀ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርክ መሠረተ ልማት የተሟላለት በመሆኑ ባለሃብቶች በፓርኩ ውስጥ ቢያለሙ ተጠቃሚ እንደሚሆኑም ነው የተመላከተው።
በፓርኩ ውስጥ አምራቾች የአቮካዶ ዘይት ማምረቻን ጨምሮ የማር፣ የወተትና የቡና ምርቶች ላይ ተሠማርተው እየሠሩ እንደሚገኙ ተገልጿል።
በየሻምበል ምህረት