የሀገር ውስጥ ዜና

በመዲናዋ በመሰረተ ልማት ላይ ጉዳት ያደረሱ ግለሰቦች በደንብ ጥሰት ተቀጡ

By Meseret Awoke

July 27, 2024

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ ክፍለ ከተሞች በመሰረተ ልማት ላይ ጉዳት ያደረሱ ግለሰቦች በደንብ ጥሰት መቀጣታቸው ተገለጸ።

ከህብረተሰቡ በደረሰ ጥቆማ መሰረት በትናንትናው ዕለት በቦሌ፣ ልደታ እና ቂርቆስ ክፍለ ከተሞች ውስጥ የደንብ ጥሰት የፈጸሙ ግለሰቦች ቅጣት የተጣለባቸው መሆኑን የመዲናዋ ከንቲባ ጽህፈት ቤት መረጃ አመልክቷል።

በዚህም መሰረትቦሌ ክ/ከተማ የኮርነርስቶን መንገድ የሠበረ አንድ ተሽከርካሪ 5 ሺህ ብር፣ ተረፈ ምርት (ቆሻሻ) በዋና መንገድ ላይ ያወረደ ተሽከርካሪ 50 ሺህ ብር መቀጣታቸው ተገልጿል።

ቂርቆስ ክ/ከተማ በእግረኛ መንገድ ላይ ሞተር ሳይክል ያቆመ ግለሰብ 3 ሺህ ብር፣ አካባቢያቸዉን ያቆሸሹ ሁለት ሱቆች በአጠቃላይ 20 ሺህ ብር እንዲሁም አካባቢውን ያቆሸሸ አንድ የፅዳት ማህበር 20 ሺህ ብር ተቀጥተዋል።

በልደታ ክ/ከተማ ደግሞ አንድ ተሽከርካሪ መንገድ የማበላሸት ተግባር በመፈፀሙ 50 ሺህ ብር መቀጣቱን ተነግሯል።