ስፓርት

ኢትዮጵያ በፓሪስ ኦሊምፒክ በቦክስ ስፖርት አትሳተፍም

By Mikias Ayele

July 26, 2024

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በ2024ቱ የፓሪስ ኦሊምፒክ ኢትዮጵያ በቦክስ ስፖርት እንደማትሳተፍ የኦሊምፒክ አዘጋጆች ቦክስ ዩኒት አስታወቀ፡፡

በፓሪስ ኦሊምፒክ የማጣሪያ ውድድር ላይ ያሸነፈው ናይጄሪያዊው ቦክሰኛ ኦሞሎ ዶላፓ ባጋጠመው የጉልበት ጉዳት ምክንያት ለፓሪሱ ኦሊሚፒክ አለመድረሱን ተከትሎ ለኢትዮጵያዊው ቦክሰኛ ፍቅረማሪያም ያደሳ ጥሪ ቀርቦለት እንደነበር ይታወሳል፡፡

በሴኔጋል ዳካር ተካሂዶ በነበረው የ2024 ኦሊምፒክ ማጣሪያ ሁለተኛ በመውጣት የብር ሜዳሊያ ያገኘው ፍቅረማሪያም ያደሳ (ጊችሮ ነብሮ) ወደ ፓሪስ ከሚያደርገው የቪዛ ጉዞ ጋር በተያያዘ በፓሪሱ ኦሊምፒክ ላይሳተፍ እንደሚችል ሲገለፅ ቆይቷል፡፡

በዛሬው እለት የኦሊምፒክ አዘጋጅ የቦክስ ዩኒት በፃፈው ደብዳቤም ዩኒቱ ፍቅረማሪያም ያደሳ (ጊችሮ ነብሮ) በሚመለከት አስፈላጊውን መረጃ ከኢትዮጵያ አለማግኘቱን ገልጿል፡፡

በዚህም በወንዶች የ57 ኪሎግራም የቦክስ ውድድር አትሌቱ መሳተፍ እንደማይችል አስታውቋል፡፡

ፍቅረማሪያም ከውድድሩ ውጭ መሆኑን ተከትሎም በፓሪሱ ኦሊምፒክ በ57 ኪሎ ግራም 17 ቦክሰኞች ብቻ እንደሚሳተፉ ዩኒቱ አስታውቋል፡፡