Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ብልጽግና ፓርቲ የበኩር ትርክትና የአጸፋ ትርክቶችን ለማስታረቅ በትኩረት እየሰራ መሆኑ ተመላከተ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ የሚታዩ የበኩር ትርክትና የአጸፋ ትርክቶችን ለማስታረቅ ብልጽግና ፓርቲ በትኩረት እየሰራ መሆኑ ተመላከተ፡፡
 
የፓርቲው ህዝብ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ከአዲስ አበባ ከተማ ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ጋር በመተባበር ያዘጋጀው 4ኛው ዙር የህዝብ ግንኙነት እና ኮሙኒኬሽን አመራሮችና ባለሙያዎች ስልጠና መድረክ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።
 
በመርሀ ግብሩ የፓርቲው ህዝብ እና ዓለምአቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋን ጨምሮ ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።
 
“የብሔራዊነት ትርክት ለኢትዮጵያ ልዕልና!!” በሚል መሪ ሀሳብ ለአምስት ቀናት በሚሰጠው ስልጠና÷ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ የኦሮሚያ፣ የአማራ እና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የኮሙኒኬሽን እና የሚዲያ አመራሮች እና ባለሙያዎች እየተሳተፉ ይገኛል።
 
መድረኩ ለቀጣይ ሀገራዊ ትርክት ግንባታው የሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎችን ሚና የሚዳስስ፣ ጠንካራና ለሀገር ክብርና ሉአላዊነት፣ ለሀገራዊ ብልፅግና ስኬት አቅም መሆን የሚችል እድል ይፈጥራል ተብሎ ይጠበቃል።
 
አቶ አዲሱ አረጋ በመድረኩ እንዳሉት፤ ከለውጡ ማግስት ጀምሮ የፖለቲካ ባህልን ለመቀየር ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው።
 
የለውጡን ምንነትና አስፈላጊነት በአግባቡ ለማስረዳትና ለማስረጽ እንዲሁም የሀገራችን ዴሞክራሲ ስርዓት በጽኑ መሠረት ላይ እንዲገነባ ለማድረግ የበኩር ትርክትን ማጎልበት አስፈላጊ መሆኑንና ለሂደቱም ወሳኝ ሚና ይጫወታል ብለዋል።
 
በኢትዮጵያ የሚታዩ የበኩር ትርክትና የአጸፋ ትርክቶችን ለማስታረቅ ብልፅግና ፓርቲ በትኩረት እየሰራ መሆኑንም ማብራራታቸውን ከፓርቲው ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
 
ሁለንተናዊ ብልጽግና በማረጋገጥ ሂደት ውስጥ የሚዲያ ባለሙያዎች የማህበራዊ ስልተ ቀመር ስልትን ባገናዘበ መልኩ በመስራት ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባም አሳስበዋል።
 
በድህረ እውነት ዘመን የሚፈጠሩ የውሽትና የፈጠራ መረጃዎችን በመከላከል የአባልና አመራሩን አቅም አሟጦ መጠቀም ይገባል ብለዋል፡፡
Exit mobile version