Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በካናዳ የተከሰተ ከባድ ሰደድ እሳት የጃስፐር ከተማን ግማሽ አወደመ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከፍተኛ የሰደድ እሳት የካናዳ የቱሪስት መዳረሻ የሆነችውን ጃስፐር ከተማ ግማሽ ያህሏን አውድሟቷል ተብሏል።
 
ጃስፐር በካናዳ ምዕራባዊ ክፍል በአልበርታ ግዛት በተራራማው የጃስፐር ብሔራዊ ፓርክ መሃል የምትገኝ ከተማ ናት።
 
ጃስፐር ከተማና ፓርኩ በዓመት ከሁለት ሚሊየን በላይ ጎብኚዎችን እንደሚያስተናግዱ ነው የተነገረው፡፡
 
እንደ አካባቢው ባለስልጣናት ገለፃ፤ ባሳለፍነው ሰኞ በግምት 10 ሺህ ነዋሪዎችና ከ15 ሺህ የሚልቁ ጎብኚዎች አደጋውን በመስጋት ከአካባቢው እንዲለቁ ተደርጓል፡፡
 
ከተማዋ ከሰደድ እሳቱ በሚመነጭ ጭስ እና አመድ የተሞላች ሲሆን÷ በየሆስፒታሉ ያሉ ታካሚዎችን የማስወጣቱ ሥራ እንደቀጠለ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
 
የአልበርታ መሪ ዳንየል ስሚት “ይህ ለማንኛውም ማህበረሰብ እጅግ የከፋ አደጋ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
 
ሰደድ እሳቱ እስከ አሁን ከቁጥጥር ውጪ መሆኑን ገልጸው÷ በአካባቢው ከ 30 እስከ 50 በመቶ የሚሆነው መሠረተ ልማት እየወደመ መሆኑን በመግለጽ ከፍተኛ የመልሶ ግንባታ እንደሚጠይቅም አክለዋል፡፡
 
ክስተቱን እየደጋገሙ አስከፊ ቅዠት የመሰለ አደጋ በማለት የጠሩት የአካባቢው ከንቲባ ሪቻርድ አየርላንድ፤ ሰዎች የሁሉም ማህበረሰብ የልብ ትርታ ናቸው ሲሉ ተናግረዋል።
 
ሰዎችን አትርፈናል ይህ ደግሞ ወሳኝ ነው፤ ከተማዋን መልሶ ለመገንባት መንገድ ማግኘት ይቻላል ያሉት ከንቲባው፤ ዳግም መገናኘትና መተቃቀፍ እንችላለን ምክንያቱም ሁላችንም ወጥተናል ማለታቸውን ዘ ኒው ዴይሊ ዘግቧል፡፡
Exit mobile version