አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የ2024 የፓሪስ ኦሊምፒክ ዛሬ ምሽት ከ2 ሠዓት ከ30 ጀምሮ “ባልተለመደ ሁኔታ” በተባለለት የተለያዩ ዝግጅቶች በፓሪስ ይከፈታል፡፡
ኢትዮጵያን የሚወክለው የመጀመሪያው የአትሌቲክስ ልዑክ ትናንት ፓሪስ መግባቱ ይታወቃል፡፡
የዛሬው የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓትም ባልተለመደ መልኩ ከስታዲየም ውጭ ሰሜናዊ ፈረንሳይን በሚያካልለው የሴይን ወንዝ እንደሚደረግ አዘጋጅ ኮሚቴው አስታውቋል፡፡
ከ206 ልዑክ የተውጣጡ ከ10 ሺህ በላይ አትሌቶችን በሴይን ወንዝ የሚያንሸራሽሩ ከ90 በላይ ጀልባዎች መዘጋጀታቸውም ተገልጿል፡፡
የፖፕ ሙዚቃ አቀንቃኞቹ ሌዲ ጋጋ፣ ሴሊን ዲዮን እና አያ ናካሙራ ምሽቱን ለማድመቅ ተዘጋጅተዋል ተብሏል፡፡
ከ300 ሺህ በላይ ሰዎች የሚሳተፉበትን የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓትም ከ1 ቢሊየን በላይ ተመልካቾች በቀጥታ ሥርጭት እንደሚከታተሉት ተጠቁሟል፡፡
በ32 የስፖርት ዓይነቶች ውድድሮች የሚካሄዱበት የፓሪስ ኦሊምፒክ እስከ ውድድሩ መቋጫ ለ3 ሺህ 800 ሠዓታት የቀጥታ ስርጭት ሽፋን እንደሚያገኝ ኮሚቴው ገልጿል፡፡