አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 18፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሲቢኢ ብር ተጠቃሚዎችቀ ቁጥር ከ11 ነጥብ 7 ሚሊየን በላይ መድረሱን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አስታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሲቢኢ ብር ፕላስ በሚል በአዲስ መልክ አሻሽሎ ያቀረበውን የሲቢኢ ብር አገልግሎት መተግበሪያ ዛሬ በይፋ ሥራ አስጀምሯል፡፡
የባንኩ ፕሬዚዳንት ተወካይ እና የሰው ኃይል ምክትል ፕሬዚዳንት ኤፍሬም መኩሪያ እንደተናገሩት ፥ የሲቢኢ ብር ተጠቃሚዎች ቁጥር ከ11 ነጥብ 7 ሚሊየን በላይ ደርሷል፡፡
ባለፈው በጀት ዓመት በባንኩ በኩል ከተፈፀመ ከ1 ነጥብ 56 ቢሊየን የሚበልጥ የገንዘብ ዝውውር ወይም በገንዘብ ከ31 ነጥብ 6 ትሪሊየን ብር በላይ ውስጥ በባንኩ ዲጂታል አገልግሎት አማራጮች የተፈፀመው 72 ከመቶ ድርሻ መያዙን ገልፀዋል፡፡
ጥሬ ገንዘብ አልባ ግብይትን እውን ለማድረግ የሲቢኢ ብር አገልግሎት እጅግ ጉልህ ሚና እንዳለውም ነው የተናገሩት፡፡
ባንኩ በዛሬው እለት በይፋ ሥራ ያስጀመረው ‘የሲቢኢ ብር ፕላስ’ መተግበሪያ በርካታ አገልግሎቶችን በማካተት ለአጠቃቀም ቀላል እና ምቹ ተደርጎ ተሻሽሎ የቀረበ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
የኢትዮጵያ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተርና የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባል ወ/ሮ ትእግስት ሃሚድ በበኩላቸው ፥ ባንኩ እንደ አንድ የፋይናስ ተቋም የዲጂታል አገልግሎትን ለሁሉም ህብረተሰብ ተደራሽ ማድረግ ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡
ባንኩ አዲስ ያቀረበው የሲቢኢ ብር ፕላስ መተግበሪያ በሚገባ በባለሙያ ተፈትሾ ደህንነቱና አስተማማኝነቱ የተረጋገጠ መሆኑን መናገራቸውን የባንኩ መረጃ ያመላክታል፡፡