አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 18፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኮሪያ ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ (ኮይካ) ለኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል፡፡
ኮይካ በሥነ-ተዋልዶና ቤተሰብ እቅድ ዙሪያ መረጃ ተደራሽ በማድረግ ግንዛቤ ማስጨበጥ የሚያስችሉ የተለያዩ የኤሌክትሮኒክስ ግብዓቶችን ለክልሎች ድጋፍ አድርጓል፡፡
በዚህም 7 ሺህ 800 ሬዲዮዎችን ጨምሮ ጀነሬተሮች፣ ስፒከሮች እና ሌሎች ግብዓቶችን ለ6 ክልሎችና ለሁለቱ ከተማ አስተዳድሮች ጤና ቢሮዎች አስረክቧል፡፡
በኮይካ የኢትዮጵያ ተወካይ ቾይ ሃን ዲዮግ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷በድጋፍ የተበረከቱት ግብዓቶች በክልሎች በሥነ-ተዋልዶና ቤተሰብ እቅድ ዙሪያ አስፈላጊ መረጃዎችን ተደራሽ ማድረግ ያስችላሉ፡፡
ድጋፉ በክልሎቹ በገጠራማ አካባቢዎች የሚስተዋለውን የእናቶች እና ህጻናት ሞት ለመቀነስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክትም አስረድተዋል፡፡
ኮይካ በኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ እና በሌሎች መስኮች የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል፡፡
ድጋፉ በወሊድ ወቅት የሚከሰትን የእናቶች እና ህጻናት ሞት ለማስቀረት የሚደረገውን ጥረት እንደሚያጠናክር የክልሎች ጤና ቢሮዎች ተወካዮች መናገራቸውንም የኮይካ መረጃ ያመላክታል፡፡